የኬንያ ዳኞችን አለባበስ የቀየረች ኢትዮጵያዊት

ዲዛይነር
አጭር የምስል መግለጫ ኮከብ ለሽልማቱ ከአምስት አፍሪካውያን ዲዛይነሮች ጋር ትወዳደራለች

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በተለይም በምርጫ ማግስት የብዙዎች ዓይን ያርፍባቸዋል።

ከነዚህ ዳኞች ጀርባ ደግሞ አንዲት ኢትዮጵያዊት አለች- ዲዛይነር ኮከብ ዘመድ።

በአውሮፓውያኑ 2013 በቅኝ ከተገዙባት ብሪታኒያ የመጣው አለባበስ የነጻይቱ ኬንያ ተምሳሌት በሆነ ልብስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀየረው ኮከብ በምትመራው ኮኪ ዲዛይንስ ነው።

በዳኞቹ ልብስ ላይ አረንጓዴው ጨርቅ የኬንያን ህገ-መንግስት ሲወክል በዙሪያው ያለው ወርቃማ ቀለም ደግሞ የፍርድ ቤቱ ህንጻ ተምሳሌት ነው።

ይህ ስራ ኮከብ ከስራዎቿ ሁሉ በጣም የምትደሰትበትና የምትኮራበት ነው። ከወራት በፊት ልብሱ በአዲስ መልክ ቢቀየርም ፈር ቀዳጅ በመሆኑ በፍርድ ቤቱ ሙዚየም ለእይታ ቀርቧል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ከነጻነት በኋላ ራሳቸውን የሚወክል ካባ መልበስ የጀመሩት በኢትዮጵያዊቷ ኮከብ በተሰራላቸው ልብስ ነው።
Image copyright TONY KARUMBA
አጭር የምስል መግለጫ ይህ የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ልብስ ለአራት ዓመታት አገልግሏል

ወደ ቤቷ ስንሄድ የተቀበለችንም ከስድሳ ዓመታት በፊት አያቷ ሲያጌጡበት በነበረው የሀገር ባህል ልብስ ላይ ባለፈው ዓመት ከሱፍ ጨርቅ ያዘጋጀችውን የአንገት ልብስ ያለውን ካባ ደረብ አድርጋ ነው።

ፋሽንና ባህል ሊነጣጠሉ አይችሉም፤ ይልቅስ አንዱ ሌላውን ይደግፋል የምትለው የኮኪ ዲዛይንስ መስራችና ባለቤት ኮከብ ዘመድ ፋሽን ባህልን ወደፊት የማሻገር ሚና የ60 ዓመታት ልዩነትን ባስታረቀ አለባበሷ ትመሰክራለች።

ናይሮቢ መኖር ከጀመረች 17 ዓመታት ቢያልፉም በመኖሪያዋም ሆነ በመስሪያ ቦታዋ ያሉት ቁሳቁሶ፣ የሃገር ባህል አልብሳትና ጥልፎች ዘወትር ከሚጎዘጎዘው ቡና ጋር ተዳምረው ከኢትዮጵያ ውጪ መሆኑን ያስረሳል።

ኮከብ ከአውሮፓውያኑ 2009 ጀምሮ ባቋቋመችው ኮኪ ዲዛይንስ የኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አልባሳትን እያዋሃደች የአፍሪካን ባህል በማስተሳሷሯ በናይሮቢ እውቅናን እያገኘች ነው።

"በእኛ ጨርቅ ላይ በመመስረት ኮትና ቀሚስ እሰራለሁ፤ ወይም ደግሞ በየቀኑ የሚለበስ ልብስ ላይ ጥለቱን ብቻ አድርጌ ከሌላ ጨርቅ ጋራ አዋህደዋለሁ፤ መጀመሪያ አልፈለግኩትም ነበር፤ ምክንያቱም ያለፈውን መሰባበር ወይም መቀየጥ ሆኖ ነበር የሚታየኝ ፤ አሁን ግን ሳስበው እንደውም ትንሽ ጥለት ኖሮት የኛንም ባህል ቢያስተዋውቅስ?" በሚል ትጠይቃለች።

Image copyright koki designs
አጭር የምስል መግለጫ የኢትዮጵያ ጥለቶች ከሌሎች ጨርቆች ጋር በቅይጥ ይሰራሉ።

ከደንበኞቿ አብዛኞቹ ኬንያውያን ናቸው፤ "የኢትዮጵያን ባህላዊ ጨርቆችና ጥለቶች በጣም ይወዷቸዋል" ትላለች ኮከብ።

ከእነዚህና ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ልብስ በተጨማሪ ደግሞ ሌሎች አፍሪካውያን የሚቀምሙላትን ባህላዊና ዘመናዊ ልብሶች ታዘጋጃለች።

ለሴቶች ፣ ለወንዶችና ለልጆች ለልዩ ዝግጅት፣ ለስራ ቦታና ለበዓላት የሚሆኑ ንድፎችን ቀርጻ በተለያዩ የፋሽን ትርዒቶች ላይ ታሳያለች፤ ለገበያም ታቀርበለች።

አሁን ደግሞ ለ2017 ምርጥ የምስራቅ አፍሪካ ዲዛይነር ሽልማት እጩ ሆና ተመርጣለች።

"እዚሁ ኬንያ የተመረቱ ጨርቆችን ተጠቅሜ አዳዲስ ዲዛይኖችን ሰርቻለሁ፤ የኢትዮጵያንም የሃገር ቤት ስሪት የሆኑ ልብሶችን ነው በአዲስ እይታና ዲዛይን የምሰራው፡ በዛ ላይ ደግሞ ከአውሮፓውያኑ 2009 እስካሁን በኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ ሆኜ መዝለቄም ለእጩነቴ መንገድ ከፍቶልኝ ይሆናል" ትላለች ውድድሩ ራሷን ወደ ዓለም ገበያ ለመቀላቀል ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላት የምትጠብቀው ኮከብ።

የሽልማቱ አላማ በኢንዱስትሪው የራሳቸውን አዲስ እይታ ተጠቅመው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ዲዛይነሮች ክብር መስጠት እንደሆነ በአዘጋጆቹ ድረገጽ ላይ ሰፍሯል።

የመገምገሚያ መስፈርቶቹ ደግሞ አዳዲስ ፈጠራ ፣ ጥሩ የዲዛይን አጨራረስ፣ የግል ምልከታ የሚታይባቸውና ለሌሎች አርአያ መሆናቸውን ይጨምራል።

ኮከብ ለዚህ ሽልማት ከኬንያ፣ ከሩዋንዳና ከታንዛኒያ እጩ ከሆኑ አምስት ሌሎች ዲዛይነሮች ጋር ትፎካከራለች።

Image copyright koki designs
አጭር የምስል መግለጫ በ2017 በሰባት የፋሽን ትርዒቶች ላይ ተሳትፋለች

የሽልማት ስነስርዓቱ በድረ ገጽ ከአድናቂዎች የሚሰጡ ድምጾች ከባለሙያዎች ዳኝነት ጋር ተዳምረው ውጤቱ መስከረም 27 ይካሄዳል።።

ታዲያ ኮከብ ባለፉት ስምንት ዓመታት ሁሉ ነገር አልሰመረላትም ፤ በተለይም በጅማሬዋ አካባቢ በዙ ተማርኩባቸው የምትለውን ስህተቶች ሰርታለች።

"መጀመሪያ የሰራሁት ልብስ አሁንም ድረስ አለ፤ በርካሽ ጨርቅ ናሙና ሰርቼ መሞከር ነበረብኝ። እኔ ግን ሳላውቅ በራሱ በሳባ ቀሚስ ሰራሁትና ጥሩ ስላልነበር ገዢ አጣ ፤ እኔም ከነኪሳራዬ ይሁን ብዬ ዝም አለኩ "

በእርግጥ እናቷ ገና በልጅነቷ ጥልፍ አስተምረዋታል ፤ እርሷም ብትሆን የተለየ ልብስ መልበስና ለልጆቿም ልብስ መስፋትን ትወድ ነበር።

ነገር ግን ይህንን እንደመዝናኛ እንጂ እንደስራ ለማሰብ ብዙ ዓመታትን ፈጅቶባታል፤ ይህም ዋጋ አስከፍሏታል።

"በራስ መተማመኑን አሰራሩንም ሆነ ቴክኒኩን ከመጀመሪያው አዳብሬው ቢሆን ኖሮ ድሮ ነበር ዲዛይነር የምሆነው። ስጀምርም እውቀቱ ስላልነበረኝ ማን ነው የሚገዛኝ? ለማንስ ነው የምሰራው? የሚለው ነገር አላሳሰበኝም ነበር "

ኮከብ በጅማሬዋ ለኬንያም ሆነ ለዘርፉ እንግዳ ነበረችና ሁኔታዎችን በአግባቡ ለመረዳት ጊዜ ወስዶባታል።

ሂደቱን ግን ያቀለለልኝ የኬንያውያን አቀባበልና አዲስ ነገር ለመሞከር ያሳዩት ፍላጎት ነው ባይ ነች- ኮከብ ።

በዚህ በመበረታታት ኮኪ ዲዛይንን ባቋቋመች በሶስተኛ ወሯ የመጀመሪያውን የፋሽን ትርዒት አቀረበች።

ኮከብ እንደምትለው ያለፉት ስምንት ዓመታት ስኬቶች ሁሌም ጅማሬያቸው ሃሳብ ነው።

"ብዙ ጊዜ ሃሳቡ ሲመጣልኝ ሌሊት ብድግ እላለሁ፤ አዲስ ነገር አስቤ ጠዋት እስክሰራው ድረስ ልቤ አትረጋም፤ ቶሎ ተነስቼ ንድፉን እስለዋለሁ።"

አጭር የምስል መግለጫ "የዲዛይን ንድፎች ሁልጊዜም ስራዬን ያቀላጥፉልኛል"

ሁልጊዜም የመጀመሪያ ስራዎቿን የምትሞክረው በራሷ ላይ ነው ። ምክንያቷ ደግሞ ደንበኞቼ ላይ የሚፈጥረውን ስሜት በትክክል እረዳበታለሁ የሚል ነው።

" ውጥን ሃሳቤ በተግባር ምን እንደሚመስል ትክክለኛ ስሜቱን አገኘዋለሁ፤ የማይንቀሳቀሱና የተዋጣ ሰውነት የተሰራላቸው ግዑዝ አሻንጉሊቶች ውበቱን እንጂ ተግባራዊነቱን አያሳዩንም "

ኮከብ ድርጅቷ ኮኪ ዲዛይንስ ከአምስት ዓመታት በኋላ ይበልጥ የተደራጀና ዘላቂ ሥራ ይዞ ምርቱን ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚያደርስ ትልቅ የፋሽን ቤት እንዲሆን ወጥናለታለች።

እስከዛው ግን እቅዶቿን በቶሎ ለማሳካት ተስፋ የጣለችበትን የ2017 የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ዲዛይነሮች ሽልማት በጉጉት ትጠብቃለች።

ተያያዥ ርዕሶች