ሳዑዲ አረቢያ ሴቶች እንዳያሽከረክሩ ጥላ የነበረችውን እገዳ ልታነሳ ነው

የሳኡዲ ሴቶች Image copyright Reuters

የአገሪቱ ሚዲያ እንደዘገበው ንጉስ ሳልማን ይፋዊ መግለጫ በመስጠት ነበር ፍቃዱን ያወጁት። የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲም እንደዘገበው ከመጭው ሰኔ ጀምሮ ውሳኔው ተግባራዊ ይሆናል።

ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ በመከልከል ሳኡዲ አረቢያ በአለም ብቸኛዋ አገር ናት። በአገሪቷ ህግ ወንዶች ብቻ ነበሩ መንጃ ፍቃድ ማውጣት የሚችሉት።

ሴቶች በአደባባይ ሲያሽከረክሩ ቢገኙ መታሰር ወይም የብር ቅጣት ይጠብቃቸው ነበር። በማያፈናፍነውም ህግ ምክንያት ብዙ ቤተሰቦች ሴቶችን ከቦታ ወደ ቦታ ለማንቀሳቀስ የግል አሽከርካሪም ይቀጥሩ ነበር።

ለአመታት የመብት ተከራካሪዎች ሴቶች ማሽከርከር እንዲፈቀድላቸው ዘመቻዎችን ቢያካሂዱም ምላሹ ህጉን በመተላለፍ ምክንያት ለእስር መዳረግ ነበር። ከነዚህም አንዷ የመብት አቀንቃኝ የሆነችው ሉጃን አል ሐትሉል ባለፈው ዓመት ለ73 ቀናት በእስር ላይ የነበረች ሲሆን ይህንንም ውሳኔ ተከትሎ "ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን" የሚል መልእክቷን አስተላልፋለች።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በኪንግ ፋህድ ስቴዲየም ገብተው ደስታቸውን እንዲገልፁ ተፈቅዶላቸዋል።

ማናል አል-ሻሪፍ "ሴቶች ለማሽከርከር" (ውሜን ቱ ድራይቭ) የሚለውን ዘመቻ አስተባባሪ ስትሆን በዚህም እንቅስቃሴዋ ለእስር ተዳርጋ ነበር። ውሳኔውንም አስመልክቶ በትዊተር ገጿ እንዳሰፈረችው "ወደ ኋላ አንመለስም" ብላለች። ሌላኛዋ አቀንቃኝ ሳሐር ናሲፍ ጂዳ ላይ ሆና ለቢቢሲ እንደተናገረችው "በጣም ተደስቻለሁ፤ ከላይ ከታች እየዘለልኩና በመሳቅ ላይ ነኝ" ስትል ደስታዋን ገልፃለች። "አሁን የማልመውን ጣሪያው ተከፋች፤ ጥቁርና ቢጫ ቀለም መኪና ነው የምገዛው" ብላለች።

በዚህ ውሳኔ ሁሉም አካል ደስተኛ አልነበረም በተለይም ወግ አጥባቂው አካል መንግሥትን የሸሪዓ ህግን አፍርሷል በማለትም ይወነጅላል። "እስከማውቀው ድረስ የሸሪዓ ምሁራን የሴቶችን ማሽከርከር የተከለከለ (ሀራም) እንደሆነ ተናግረዋል። እንዴት አሁን ተፈቀደ?" በማለት አንድ ግለሰብ ትችቱን በትዊተር ገፁ አስፍሯል።