በኢሬቻ በዓል ላይ ባልተለመደ መልኩ የትኛውም የመንግሥት አካል ድርሻ አይኖረውም ተባለ

የበዓሉ ተሳታፊ ወጣቶች Image copyright Amensisa Ifa

በዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ላይ የታጠቀ የመንግሥት ኃይል እና ባለስልጣናት መንግሥትን ወክለው አይገኙም ተባለ።

እሁድ በሚካሄደው የኢሬቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የታጠቀ የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪ ኃይል እንደማይገኝ በዓሉን እያስተባበረ የሚገኘው የኦሮሚያ አባገዳዎች ምክር ቤት ገልጿል።

በመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች ቦታም 300 በጎፍቃደኛ ወጣቶች ሥርዓት ያስከብራሉ ሲሉ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የሆኑት አባ ገዳ በየነ ሰምበቶ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

''በዘንድሮው በዓል ላይ የትኛውም የመንግሥት አካል ምንም አይነት ድርሻ አይኖረውም፤ የመንግሥት ባለስልጣናትም ንግግር አያደርጉም ።'' ሲሉ ተናግረዋል።

''የመንግሥት ባለስልጣናት እንደማንኛውም ዜጋ በበዓሉ ላይ የመሳተፍ መብት አላቸው። ከዚህ የዘለለ ግን ሌላ ተሳትፎ አይኖራቸውም'' ሲሉ አባ ገዳ በየነ ሰምበቶ አስረድተዋል።

በዓሉ በሚከበርበት ቦታ ያሉ የመግቢያና የመውጫ መንገዶችን የማስፋት ሥራዎች እንደተከናወኑ አባ ገዳ በየነ ተናግረዋል።

ከዓመት በፊት በተካሄደው የኢሬቻ በዓል ላይ የፀጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ በርካታ ሰዎች ሲሸሹ ጉድጓድ ውስጥ ገብተውና ተረጋግጠው ህይወታቸው ማለፉ ያታወሳል።

የክልሉ የፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ቃለ-አቀባይ የሆኑት አቶ መለሰ ተፈራ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በአባ ገዳዎች የተመለመሉ በጎፍቃደኛ ወጣቶች የበዓሉን ሥነ-ሥርዓት ያስከብራሉ። የኦሮሚያ ፖሊስ ወደ ቢሾፍቱ የሚወስዱ መንገዶችን ብቻ ይቆጣጠራል፤ ያሉት አቶ መለሰ ''መሳሪያ የታጠቀ ፀጥታ አስከባሪ ኃይል በበዓሉ ስፍራ አይገኝም'' ሲሉ አረጋግጠዋል።

''በድንገት''

ከዓመት በፊት በኢሬቻ በዓል ላይ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች በቢሾፍቱ ከተማ በቆመላቸው የመታሰቢያ ሃውልት ላይ ''በድንገት ህይወታችውን ላጡ'' ተብሎ የሰፈረው ጽሁፍ በበርካቶች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮ ነበር።

አባ ገዳ በየነ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ ''በድንገት'' የሚለው ጽሁፍ እንዲፋቅ ተገርጓል። በበዓሉ ዋዜማም ህይወታቸውን ላጡት የህሊና ጸሎት እንደሚደረግ ጨምረው አስረድተዋል።

የኢሬቻ በዓል ምንድን ነው?

የቀድሞ የቱለማ አባ ገዳ ነጋሳ ነገዎ ''ኢሬቻ የምስጋና ቀን ነው። ለፈጣሪ የሚሰጥ ምስጋና''።

''ክረምቱን አሳለፍከን፣ ወደ ሌላ ዘመን አሸጋገርከን፣ የዘራነው አሽቷል በማለት የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድበን ከሁሉም አቅጣጫ በመሰባሰብ እርጥብ ሳር በመያዝ ለዋቃ ምስጋና እናደርሳለን'' ሲሉ ያስረዳሉ።

የኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ከተማ በሆር ሃርሰዴ የሚከበር ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በበዓሉ ላይ ይሳተፋል።

ተያያዥ ርዕሶች