'ዕውቀት ሳያገኙ ትምህርት ቤት መመላለስ'

ተማሪዎች በትምህርት ቤት Image copyright Sean Gallup

ዕድሜያቸው በአስራዎቹ ውስጥ ከሚገኙ 10 ህጻናት መካከል ስድስቱ መሠረታዊ የትምህርት ክህሎት እንደሌላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ይፋ አደረገ።

ድርጅቱ ጥናቱን 'አስደንጋጭ' እና 'የትምህርትን ቀውስ' የሚያሳይ ብሎታል።

በግጭት ውስጥ ባሉ ወይንም ከሰሃራ በታች በሚገኙ ደሃ ሃገራት ውስጥ በትምህርት ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም ላይ አትኩረዋል።

ሆኖም በዩኔስኮ የስታትስቲክስ ተቋም የተደረገው ጥናት እንደሚያሳው በትምህርት ቤቶቹ የትምህርት ጥራት ችግር ይስተዋላል።

ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሆነው 600 ሚሊዮን ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች መሠረታዊ የሂሳብም ሆነ የማንበብ ክህሎታቸው ዝቅተኛ መሆኑ ነው።

ከፍተኛ ልዩነት

እንደጥናቱ ከሆነ ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት ከሚገኙ ህጻናትና ታዳጊዎች መካከል 88 በመቶ የሚሆኑት መሠረታዊ የማንበብ ክህሎት ሳይኖራቸው ወደ ጉርምስና ይሸጋገራሉ።

Image copyright World Bank
አጭር የምስል መግለጫ ሱዳን ውስጥ ያለ ትምህርት ቤት

ሪፖርቱ ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚመጣው የተማሩ ሰዎች ቁጥር ሲጨምር መሆኑን ይገልጻል።

"እነዚህ ልጆች ከመንግሥታቸው ወይም ከማህበረሰባቸው የተሸሸጉ አይደሉም። እንደውም በትምህርት ቤት ነው የሚገኙት" ሲሉ የዩኔስኮ የስታትስቲክስ ተቋም ዳይሬክተር ሲልቪያ ሞንቶያ ይገልጻሉ።

Image copyright World Bank
አጭር የምስል መግለጫ የላኦስ ተማሪዎች

የዓለም ባንክም ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት "ዕውቀት ሳይገበዩ በትምህርት ቤት መገኘት" በሚል እያጋጠመ ስላለው ችግር ይፋ አድርኋል።

እንደጥናቱ ከሆነ በኬንያ፣ ታንዛንያ እና ኡጋንዳ የሚገኙ ተማሪዎች ለዓመታት በትምህርት ቤት ቆይተውም ቀላል ቁጥሮችን መደመርም ሆነ ቀላል ዓረፍተ ነገሮችን ማንበብ ይቸገራሉ።

ችግሩ ምንድን ነው?

Image copyright UN Photo
አጭር የምስል መግለጫ ብዙ ህጻናት ትምህርት ቤት የሚገኙት ለትምህርት ሚያስፈልጋቸውን በሙሉ አሟልተው አይደለም።

የዓለም ባንክ ጥናት የችግሩን ምንጭም ለመለየት ሞክሯል፡

  • ብዙ ህጻናት ትምህርት ቤት የሚገኙት ለትምህርት የሚያስፈልጋቸውን በሙሉ አሟልተው አይደለም።
  • የተማሪዎቹ ቤተሰቦች በድህነት የሚኖሩ ስለሆነ ብዙዎች የምግብ እጥረትና የጤና ችግር አለባቸው። ይህም በአካልም ሆነ በአዕምሮ ለትምህርት ብቁ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል።
  • መምህራን በቂ ዕውቀት ስለማያገኙ ብቃት ያላቸው መምህራን ቁጥር አነስተኛ ነው
  • መምህራን ክፍያ በጊዜው ስለማያገኙ ብዙ ጊዜ ከትምህርት ቤት ይቀራሉ

የዓለም ባንክ ዋና የኢኮኖሚ ባለሙያ ፖል ሮመር እንደሚሉት ብዙ ልጆች ትምህርት ቤት ገቡ ማለት ሙሉ ለሙሉ በቂ ዕውቀት እያገኙ ነው ብሎ መታመን የለበትም።