የአውሮፓ ህብረት ህጋዊ የስደተኞች ዕቅድ ይፋ አደረገ

ስደተኞች በባህር ላይ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ አዲሱ ዕቅድ በህገ ወጥ ደላሎች ህይወታቸው ለአደጋ የተጋለጡትንም ለመርዳት አልሟል

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ቢያንስ 50 ሺህ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ ለመውሰድ የሚያስችለውን የሁለት ዓመት ዕቅድ አዘጋጀ። የምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት ከዕቅዱ ቀዳሚ ተጠቃሚዎች መካከል ይሆናሉ ተብሏል።

የኮሚሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ፌደሪካ ሞጌሪኒ "ዕቅዱ ጊዜያዊ መፍትሄ ሳይሆን እጅግ ውስብስብ ለሆነው የወቅቱ ችግር እልባት ለመስጠት የታለመ ነው" ብለዋል።

ዕቅዱ በ 28ቱ የህብረቱ አባል ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት አላልቶታል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም በሁለት ዓመት 160 ሺህ ስደተኞችን ለማስተናገድ የተያዘው ዕቅድ ከአንድ አምስተኛ በታች የሆነውን ብቻ በተግባራዊ በማድረግ በመጪው ሳምንት ይጠናቀቃል።

የምሥራቅ አውሮፓ ሃገራት በተለይም ፖላንድና ሃንጋሪ ውሳኔውን በመቃወም ፍርድ ቤት ቢሄዱም፤ የአውሮፓ ፍትህ ፍርድ ቤት ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ አዲሱ ዕቅድ ለስደተኞች ህጋዊ ከለላ የሚሰጥ ሲሆን አፍሪካንም አካቷል

ሊጠናቀቅ ቀናት የቀሩት ነባሩ የስደተኞችን ዕቅድ እ.አ.አ ከ2014 ጀምሮ ወደ አውሮፓ የገቡትን 1.7 ሚሊዮን ስደተኞች ለመቀበል ታስቦ የተጀመረ ነው።

ዕቅዱ ስደተኞች በደረሱበት ሃገር ጥገኝነት መጠየቅ አለባቸው የሚለውን የአውሮፓ ሃገራት ህግ ያስቀረ ነው። ይህም ወደ አውሮፓ ለሚገቡ ስደተኞች እንደ መግቢያ የሆኑትን የጣሊያንና የግሪክን ጫና ለመቀነስ ያለመ ነው።

በተግባር ላይ ለነበረው ዕቅድ አለመሳካት በ2016 በቱርክና በአውሮፓ ህብረት መካከል በተደረገው ስምምነት መሰረት፤ በሊቢያ በኩል የሚገቡት የስደተኞች ቁጥር በመቀነሱና በቅርቡም ወደአውሮፓ የገቡት ሰዎች በዕቅዱ ውስጥ ከታቀፉ ሃገራት ባለመምጣታቸው ነው።

በኮሚሽኑ የተዘጋጀው አዲሱ የሁለት ዓመት ዕቅድ፤ እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ አደጋ ያንዣበባቸውን ሰዎች ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከቱርክ ከማካተቱም በላይ ለሰሜንና የምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት ዜጎችም ትኩረት ሰጥቷል።

"ይህ ዕቅድ በህገ-ወጥ ደላለሎች ህይወታቸው አደጋ ላይ ለወደቀ ሰዎች ህጋዊና ደህንነታቸው የሚያስጠብቁ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የተጀመሩ ሥራዎች አካል ነው" ተብሏል።

ማሳሰቢያ፡ ቢቢሲ ስደተኞች ሲል ጉዳያቸው ገና በሂደት ላይ ያሉና የመኖሪያ ፈቃድ ያላገኙ ሰዎችን በሙሉ ያጠቃልላል። ይህም እንደ ሶሪያ ካሉ ሃገራት የሚመጡ የመኖሪያ ፈቃድ የማግኘት ዕድል ያላቸውንና ለተሻለ ራና ኑሮ የሚሰደዱ የኢኮኖሚ ስደተኞችን ያጠቃልላል።