በአንድ ቦታ የተሰበሰቡ ሰዎችን ቁጥር እንዴት ማወቅ ይቻላል?

airport queue Image copyright Getty Images

በተለያየ ምክንያት በአንድ ቦታ የተሰባሰቡ ሰዎችን ቁጥር መገመት ብዙ ጊዜ አከራካሪ ርዕስ ይሆናል።

በኢትዮጵያም በበዓላት፣ በፖለቲካ ስብሰባዎችና ሠልፎች እንዲሁም በሌሎችም ጉዳዮች በአንድ ቦታ የተሰባሰቡ ሰዎች ቁጥር በተደጋጋሚ ውዝግብ ሲፈጥር ይስተዋላል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ከተገኘው የህዝብ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የመገናኛ ብዙሃንን ሲተቹ ቆይተዋል።

ትራምፕ ወቀሳውን ያቀረቡት በቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙ ሰዎች በቁጥር ይበልጣሉ በሚል መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸውን ተከትሎ ነው።

ትራምፕ በዓለ ሲመታቸው ላይ የተገኘው የህዝብ ብዛት 1.5 ሚሊዮን ነው ቢሉም መገናኛ ብዘሃን ግን ቁጥሩን ከ500 ሺህ ብዙም ያልዘለለ ነው ይላሉ።

ስለዚህ በአንድ ቦታ የተሰበሰቡ ሰዎችን ቁጥር ለማወቅ እንዴት ማስላት እንችላለን?

ባለሙያዎች እንደሚሉት በአንድ ቦታ የተሰባሰቡ ሰዎችን ቁጥር በትክክል ማወቅ ይከብዳል።

በተለይ ደግሞ ሰዎች በሚንቀሳቀሱበት እና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ሲሰባሰቡ ቁጥሩ ለፕሮፖጋንዳ ተግባር ስለሚውል በተቃራኒ ቡድኖች መካከል የውዝግብ ምንጭ ይሆናል። ባለሙያዎች ይህንን ለማስታረቅ የሚረዱ የተለያዩ ዘዴዎች እንዳሉ ይጠቁማሉ፡

1. መሠረታዊ ጥያቄዎችን ይጠይቁ

ስፖርታዊ ውድድሮችን ወይም የሙዚቃ ኮንሰርቶችን የሚታደሙ ሰዎች ብዛት በቀላሉ የሚታወቅ ነው።

የተዘጋጁ ቲኬቶች ብዛት ከመታወቁም በላይ ሰዎች ወደ ቦታው ሲሄዱ ተቆጥረው መግባት ይችላሉ።

ወደ ቦታው ሰዎችን ያጓጓዙ ባቡሮች እና መኪናዎች ትኬቶች ቁጥርም ሌላው መለኪያ ሊሆን ይችላል።

2. የቦታውን ስፋትና መያዝ የሚችለውን ቁጥር ማስላት

የሚሰበሰቡት ሰዎች የሚይዙትን ቦታ መጠን ማወቅ አስፈላጊ ነው።

ይህን ለማወቅ ካርታ መጠቀም ወይም ሰዎቹ የተሰባሰቡበትን ቦታ ከመሰባሰባቸው በፊት ወይንም በኋላ በመለካት ማወቅ ይቻላል። ሰዎቹ በሚሰባሰቡበት ወቅት የያዙትን ቦታ በትክክል ማወቅ ከፍተኛ እገዛ አለው።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ እዚህ ፎቶ ላይ ምን ያህል ስዎች ይታያሉ?

3. የጃኮብስ ክራውድ ቀመርን ተግብ

ይህ ቀመር ሰዎች የተሰባሰቡበትን ቦታ በአራት ማዕዘኖች በመከፋፈል እያንዳንዱ አራት ማዕዘን ምን ያህል ሰው እንደሚይዝ ማስላት ነው።

ቀመሩ ጋዜጠኛ በሆነው ፕሮፌሰር ሄርበርት ጃኮብስ የተሰራ ሲሆን በዚሁ መሠረትም አነስተኛ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ፤ አንድ ካሬ ሜትር አንድ ሰው ይይዛል።

በሌላ በኩል ብዙ ሰው በተሰበሰበበት አንድ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ 2.5 ሰዎች ሲኖሩ እጅግ የበዛ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ ላይ ደግሞ በአንድ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አራት ሰዎች ተጨናንቀው ሊኖሩ ይችላሉ።

4. ፎቶ መጠቀም

ክፍተኛ ጥራት ያለውና ከሰማይ ላይ ወይንም ከሳተላይት የተነሳ ፎቶ በቀላሉ በርከት ብለው የተሰበሰቡ ሰዎችን ለመቁጠር ያስችላል።

ሰዎችን በራሱ ቆጥሮ ውጤቱን ይፋ ለማድረግ የሚያስችል ሶፍት ዌርም ተግባራዊ ተደርጓል።

ካልሆነም አሁንም የጃኮብስን ቀመር ተግባራዊ ይደረጋል።

ፎቶን መጠቀም አስቸጋሪ የሚያደርገው ነገር ቢኖር የሰዎች ቁጥር በየጊዜው ተለዋዋጭ ከሆነ ነው።

ይህ ከሆነ ደግሞ ሰዎች በተነሳው ፎቶ ላይ በዝተው ወይንም አንሰው ሊታዩ ይችላሉ። በተጨማሪም ሰዎች በጨለማ፣ በህንጻዎች፣ በዛፎች እና በሌሎች ምክንያቶች ካሜራ ውስጥ ላይገቡ ይችላሉ።

5. የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ለመቁጠር አንድ ቦታ ላይ በመሆን የመቁጠር ዘዴን ይጠቀሙ

ሰዎች ተሰብስበው የሚያልፉበት አማካይ ቦታ ላይ በተወሰነ ሰዓት የሚያልፉ ሰዎችን መቁጠር። በዚህ መሠረት ሁሉም ሰው የሚያልፍበትን የጊዜ መጠን በመለየት ምን ያህል ሰዎች እንደተሳተፉ ማወቅ ይቻላል።

እነዚህ ሁሉ ዘዴዎች ትክክለኛ ቁጥር ባይሰጡም ለመገመት ግን ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ።