ስቴፈን ፓዶክ : ቁማርተኛና የቀድሞው የሂሳብ አያያዝ ባለሙያ

Stephen Paddock Image copyright CBS News

የላስ ቬጋስን ጥቃት የፈጸመው የቀድሞው የሂሳብ አያያዝ ባለሙያ ስቴፈን ፓዶክ ሃብታምና በጡረታውም የተመቻቸ ሕይወት የነበረው ሰው ነው።

የ64 ዓመቱ ፓዶክ የአውሮፕላን አብራሪነት ፈቃድ ሲኖረው የሁለት አነስተኛ አውሮፕላኖች ባለቤት ነበር።

ለአደንም ህጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶታል፤ ከዚህ ቀደም ግን ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ እንዳልነበረበት ፖሊስ አስታውቋል።

አንድ የቀድሞ ጎረቤቱ ተጠርጣሪውን ቁማርተኛና ወጣ ያለ ባህሪ የነበረው ሲሉ ገልጸውታል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ለሮይተርስ እንዳሉት ግለሰቡ ስነልቦናዊ ችግር እንደነበረበት የሚያሳዩ ሁኔታዎችም አሉ።

ጥቃቱ በኦርላንዶ 49 ሰዎች ከሞቱበትና በወቅቱ የከፋ ከተባለው አደጋ ልቆ በአሜሪካ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ከተፈጸሙት ሁሉ በላይ ደም አፋሳሽ ሆኗል።

Image copyright CBS News
አጭር የምስል መግለጫ ''ከሌለው ጎረቤትህ ጋር የመኖር ያህል ነበር'' የቀድሞ ጎረቤቱ

ፓዶክ ማንዳላይ ቤይ ሆቴል ላይ ሆኖ በከፈተው ተኩስ ቢያንስ 59 ሰዎችን ገድሎ ከ 500 በላይ የሚሆኑት ካቆሰለ በኋላ ራሱን አጥፍቷል።

ፖሊስ የላስ ቬጋሱ ታጣቂ ጥቃቱን ለመፈፀም ምን እንዳነሳሳው እያጣራ ነው።

ፖሊስ ካለፈው ሃሙስ ጀምሮ ባረፈበት የሆቴሉ 32ኛ ፎቅ ላይ በሚገኝ ክፍል ውስጥ 23 መሣሪያዎችን አግኝቷል።

በመኖሪያ ቤቱም ተጨማሪ 19 የጦር መሳሪያዎች፣ በግቢውና በመኪናው ውስጥ ደግሞ ፈንጂዎች ተግኝተዋል።

መሣሪያዎችን የሸጠለት ሰውም ፓዶክ የአሜሪካን የምርመራ ቢሮ የማንነት ማጣሪያ ጨምሮ ሁሉንም የመግዣ መስፈርቶች አሟልቶ ስለተገኘ እንደሸጠለት ተናግሯል።

''ሆኖም ከኔ የገዛቸው መሣሪያዎች ማሻሻያ ሳይደረግላቸው በቪዲዮ የተመለከትናቸውና የሰማናቸውን አይነት አቅም ሊኖራቸው አይችልም '' ብሏል።

አይ ኤስ ለጥቃቱ ኃላፊነትን ቢወስድም የአሜሪካ የምርመራ ቢሮ( ኤፍ ቢ አይ) ግን እስካሁን ፓዶክ ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንደነበረው የሚያሳይ ምንም መረጃ አላገኘም።

አጭር የምስል መግለጫ ጥቃቱ የተፈጸመበት አካባቢ

አባቱም የባንክ ቤት ዘራፊ እንደነበር፣ በምርመራ ቢሮ እጀግ ተፈላጊ ወንጀለኞች ዝርዝር ውስጥ ሰፍሮ እንደነበረና በአንድ ወቅትም ከእስር ቤት ማምለጡን ታናሽ ወንድሙ ኢሪክ ፓዶክ ለጋዜጠኞች ተናግሯል።

ፓዶክ በ 2016 ነበር ከ62 ዓመቷ የሴት ጓደኛው ማሪሎ ዳንሌይ ጋር በአሁኑ መኖሪያ ቤቱ መኖር የጀመረው።

ማሪሎ ከጥቃቱ በኋላ በፖሊስ ስትፈለግ ቆይታ በጃፓን ብትገኝም እጇ እንዳለበት የሚያሳይ ምንም ማስጃ አልተገኘባትም።

Image copyright Police handout
አጭር የምስል መግለጫ መጀመሪያ በግብረ አበርነት ተፈላጊ የነበረችው ማሪሎ ዳንሌይ ከአሜሪካ ውጭ ተግኝታለች

ሆቴሉን ሲከራይም ከእርሱ ጋር አልነበረችም ብሏል ፖሊስ። እንዲያውም ፓዶክ መታወቂያዋን ለአላማው ሲጠቀምበት ነበር።

የቀድሞ ጎረቤታቸው ዳያን ማኬይ ለዋሽንግተን ፖስት ጥንዶቹን ሁልጊዜም ነገሮችን በምስጢር ማድረግ የሚያዘወትሩ በማለት ገልጸዋቸዋል።

" ወጣ ያለ ባህሪ ነበረው ፤ሁሉንም ነገር በምስጢር ይይዝ ነበር ፤ ከሌለው ጎረቤትህ ጋር የመኖር ያህል ነው'' ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ