የገጠር ሴቶች በግብርና ስራ የተደቀነባቸውን ጋሬጣ እያለፉ ነው?

የጃፓን ሴት አርሶአደር Image copyright BEHROUZ MEHRI / AFP

ባለፉት አስርት ዓመታት በታዳጊ ሀገራት በግብርና ተግባራት ላይ የሚሳተፉ ሴቶች ቁጥራቸው ጨምሯል።

የስራ ሁኔታዎቻቸውን ለማሻሻል የሚረዱ መርሃግብሮችም እየተተገበሩ ነው።

ግን ይህ እርምጃ እውን በተጨባጭ እያበቃቸው ነው ?

"ብዙ የስኳር ድንች ምርት አለን የምንፈልገው ገዢ ብቻ ነው።" ትላለች ሮዛሊና ባሌስቴሮስ

በሰሜናዊ ኮሎምቢያ ዳርቻ የምትገኘው ኮረብታማዋ ሞንቴስ ዴ ማርያ ለሮዛሊና የመኖሪያም የመስሪያም ቦታዋ ናት።

በዚህ ዓመት ደግሞ ጥሩ ምርት አግኝተዋል፤ ነገር ግን የግዢ ፍላጎቱ አነስተኛ ስለሆነ ምርቱ ከወዲሁ መበስበስ ጀምሯል።

እናም ማህበረሰቡ ዩ ቲዩብ ባሉ ማህበራዊ ድረ-ገፆች የሽያጭ ጥሪ ማሰማት ጀምሯል።

"ድንች ስኳራችንን በመሸመት እንድትረዱን እንጋብዛለን።" ትላለች አርሶ አደሯ በኮሎምቢያ ዝናን ባተረፈው የ40 ሰከንድ ቪዲዮ።

'' ለመገጣጠሚያ ህመም ፣ለሆድ ድርቀትና በማረጫ ወቅት በጣም ጠቃሚ ምግብ ነው።" በማለት ሌሎች የስራ ባልደረቦቿም ምርቶቻቸውን ያስተዋውቃሉ።

Image copyright Fundacion Semana / YouTube
አጭር የምስል መግለጫ የኮሎምቢያ ሴት አርሶአደሮች በዩቲዩብ ምርቶቻቸውን እያስተዋወቁ ነው

የ32 ዓመቷና የ 5 ልጆች እናት የሆነችው አርሶአደር አይናጉል አብድራህማኖቫም በማዕከላዊ ኪርጊስተን በሚገኘው ተራራማ መንደር በሚገኝ የሴቶች ራስ አገዝ ቡድን ታቅፋለች።

"በተከላውም ሆነ በጠብታ መስኖ አጠቃቀም ብዙ አግዘውኛል" ትላለች ።

ከዚህ ቀደም በእርሻ መሬቷ እንደማይለሙ የምታስባቸውን ቲማቲም፣ ኪያርና ካሮት ታመርታለች።

በሰሜናዊ ላኦስ ደግሞ ወይዘሪት ቪዬንግ በእንጉዳይ ምርት ገቢ ኑሮዋንም ትመራለች።

ማህበረሰቡ የጫካ እንጉዳዮችን ለምግብ ፍጆታ የመሰብሰብ ልምድ ነበረው።

ወይዘሪት ቪዬንግና ሌሎች ጎደኞቿ በአካባቢው ለገበያ የሚቀርብ እንጉዳይን የማልማት ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ግን ነገሮች መቀየር ጀመሩ።

Image copyright FAO / Oscar Castellanos
አጭር የምስል መግለጫ ቪንግ በግብርናና ብዝኃ ሕይወት ፕሮጀክት የእንጉዳይ ልማት ቲክኒኮችን ተምራለች

የታዳጊ ሀገራት ሴቶች ከግብርና የሰው ኃይል በአማካይ 43 በመቶውን ይሸፍናሉ።

ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ደግሞ ባለሙያዎች በግብርና ሴቶች ከዚህ በተሻለ የሚሳተፉበትን ሂደት አስተውለዋል።

የግብርና ስራ ወደ ሴቶች እየተሸጋገረ ስለመሆኑ አሳማኝ ማስረጃዎች እንዳሉ በ2016 የወጣው የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ሪፖርት ያመለክታል።

ምናልባትም ወንዶች ከግብርና ስራዎች እየወጡ ስለሆነ አሊያም ሴቶች በዘርፉ በሚገኙ ተግባራት እየተሳተፉ ስለሆነ ሊሆን ይችላል።

ዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት በ2015 በዓለማችን በኢኮኖሚ በንቃት ከሚሳተፉ ሴቶች አንድ አራተኛ የሚሆኑት በግብርና የተሰማሩ እንደነበሩ ይገልጻል።

ይሁንና ይህ አሃዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ እንደየአካባቢው ሁኔታ ልዩነት ያሳያል።

አነስተኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት ግብርና ከፍተኛውን የስራ እድል ቢፈጥርም ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ግን ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ወደ ኢንዱስትሪ ወይም ወደ አገልግሎት ዘርፍ ያመዝናሉ።

ታዲያ ለውጡ የሚታየው የት ነው?

ይህ የሴቶች የግብርና ተሳትፎ በሰሜናዊ አፍሪካ በይበልጥ ይስተዋላል ፤ በግብርና የተሰማሩ ሴቶች ቁጥር እአአ 1980 እስከ 2010 በነበሩት 30 ዓመታት ከ 30 በመቶ ወደ 43 በመቶ አድጓል።

በምዕራብ እስያ በዚሁ ጊዜ ከ 35 ወደ 48 በመቶ ጨምሯል።

የሴቶች የግብርና ተሳትፎ በምስራቅና በደቡብ ምስራቅ እስያ እንዲሁም በላቲን አሜሪካም ቢሆን ለውጡ በግልጽ የሚታይ ነው።

ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ግን ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በሴቶች ተሳትፎ ብዙም ለውጥ አልታየም።

በሴራሊዮን፣ በሌሴቶና በሞዛምቢክ ግን ተሳትፎው ከ 60 በመቶም በልጧል።

የግብርና ባለሙያዎች በዚህ አካባቢ ከወዲሁ የግብርና ስራውን ሴቶች እንደተቆጣጠሩት አረጋግጠዋል።

የወንዶች ስደት የፈጠረው ጫና

የሴቶች የእርሻ ስራ ተሳትፎ መጨመር በራሱ ልማት ሊሆን ይችላል።

አንዳንዶች እርሻን ጉሮሮን ከመሸፈኛ አልፈው እንደገቢ ምንጭ በመጠቀም ቤተሰባቸውንና ማሀበረሰባቸውን እየደጎሙ ነው።

ሆኖም ይህ ሁልጊዜም የሴቶችን መብቃት ላያሳይ ይችላል።

ለዚህ ከዋነኛ ምክንያቱ አንዱ የወንዶች ስደት የፈጠረው ጫና ነው።

"የገጠር ወጣት ወንዶች ከሴቶቹ በበለጠ ወደ ከተማ ይሰደዳሉ'' ይላሉ የፋኦ የፖሊሲ ባለሙያው ሊበር ሰቶሉካል።

'' የሴቶች ተሳትፎ በከፊል ወይም ካልታረሰ የእርሻ መሬት አቅርቦት ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፤ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች አዋጪ የስራ አማራጮች መኖራቸውና ግጭቶችና ጦርነቶች በወንዶች የህዝብ ብዛት ትልቅ ተጽዕኖ ፈጥረዋል''

እናም ቤት የቀሩ ሴቶች የወንዶቹን እጥረት ለማካካስ የስራ ሰዓታቸውን መጨመር ግድ እንደሚላቸው ሞያተኞች ይናገራሉ።

ሴቶች በግብርና የሰው ኃይል ትልቅ ድርሻ ቢኖራቸውም በገጠር ሊያገኙ የሚችሉት የስራ ዕድል ግን አሁንም በስጋት ላይ ነው።

ብዙዎቹ ክፍያ የሌላቸው፣ በተወሰነ ወቅት ብቻ የሚኖሩና በትርፍ ጊዜ ሊሰሩ የሚችሉ ናቸው።

ክፍያ ባላቸው ስራዎችም ቢሆን ትኩረታቸው በጉልበት ስራና ብዙም ክህሎት በማይጠይቁት ሲሆን የአስተዳደር ቦታዎች ግን በአብዛኛው የሚያዙት በወንዶች ነው።

"ሴቶች ቢያርሱም የገበያ ስራውን የሚከውኑትና ገንዘቡን የሚቆጣጠሩት ወንዶች ናቸው። '' የምትለው ደግሞ የማህበራዊና የስነጾታ ባለሙያዋ ዲና ናጃር ናት።

የክፍያ አለመመጣጠን

ሴቶች ከወንዶች ጋር ተመሳሳይ ስራ ሲሰሩም የሚከፈላቸው ክፍያ ያነሰ ነው።

በ14 ሀገራት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ደሞዛቸው ከወንዶቹ በአማካይ በ28 በመቶ ይቀንሳል።

የታዳጊ ሀገራት ሴት አርሶአደሮች ደግሞ ሌሎች ኃላፊነቶችም ስለሚበዙባቸው ከ 20-30 በመቶ የምርታማነት ከፍተት እንደሚታይባቸው ባለሙያዎች ያናገራሉ።

ሆኖም በነዚህ ሁኔታዎች ውስጥም አልፎ የሴቶች የግብርና ሚና ተጨባጭ ጥቅሞችን አስገኝቷል።

Image copyright FAO / Nadege Boro
አጭር የምስል መግለጫ ''በተለይም በዘር ጊዜ ህይወት በጣም አስቸጋሪ ነበር'' አርሶአደር ሳኒሃን

''አሁን ምርት የመሰብሰቢያ ጊዜ ባይሆንም አልጨነቅም፤ በከባድ ጊዜም በሚያጠነክሩን አዳዲስ መስኮች እየተሳተፍን ነው።'' ባይ ናት በማዕከላዊ ማሊ የገጠር መንደር የምትኖረው የ4 ልጆች እናት ሳኒሃን ቴራ።

በፋኦ እገዛ በተማሯቸው አዳዲስ ቴክኒኮች እሷና መሰል የማሊ ሴቶች ወንዶች ወደሌላ የስራ ዘርፎች ሲሰማሩ ቤተሰባቸውን የመመገብና ሙሉ መሬታቸው ላይ ተክሎችን የማልማት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ።

"በእርግጠኝነት የምናገኘው ምርት የምግብ ፍጆታችንን ለበርካታ ወራት እንደሚሸፍንልን አልጠራጠርም።'' ትላለች ሳኒሃን።

ይሁንና የመሬት ባለቤትነት መብት ጉዳይ ለዚህ ማህበራዊ እድገት ትልቁ ማነቆ ሆኗል።

ምክንያቱም ከታዳጊ ሀገራት በብዙሃኑ ሴቶች ከወንዶች እኩል የመሬት ባለቤት የመሆን መብት የላቸውም።

100 ሴቶች የተሰኘው ተከታታይ መሰናዶ አምስት ዓመት ሆነው። በዓለም ዙሪያ ያሉ ሴቶች ሊወያዩባቸው በሚፈልጓቸው ርዕሶች ላይ ያተኩራል። በዚህ ዓመትም ሴቶች ለአራት ዋና እንቅፋቶች የሚያቀርቡትን መፍትሔዎች ይዳሰሳሉ።

እነሱም: ከባድ ፈተናዎች፣ የትምህርት እጦት፣ በሕዝብ መጓጓዣ ላይ ሚፈፀም ጥቃት እንዲሁም ፆታዊ ጭቆና

በተከታታይ ከሚቀርቡት የ100 ሴቶች መሰናዶዎችን ይከታተሉ።