ጥቃት የተፈጸመባቸው በፓርላማው መንግስትን በመቃወም የሚታወቁ ግለሰቦች ናቸው

Bobi WIne Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ዘፋኙ ሮበርት ክያጉላንዪን ባለፈው ሰኔ ነው ምርጫ በማሸነፍ የፓርላማ አባል መሆን የቻለው

ወደ ፖለቲካው ዓለም የተቀላቀለውን ዘፋኙን ሮበርት ክያጉላንዪን ጨምሮ ሁለት የኡጋንዳ ተቃዋሚ የፓርላማ አባላት ቤቶች ላይ በደረሰ ፍንዳታ ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

በአድናቂዎቹ ዘንድ ቦቢ ዋይን በሚል ስሙ የሚታወቀው ክያጉላንዪን "ጥቃቱ የተፈጸመብኝ ገዢው ፓርቲ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የዕድሜ ጣሪያ እንዲነሳ ያቀረበውን ሃሳብ በመቃወሜ" ነው ብሏል።

የክያጉላንዪን እና የአለን ስሴዋንያና ቤቶች ላይ ጥቃት የደረሰው ማክሰኞ ማለዳ ነው።

መንግሥት ከፍንዳታው ጀርባ እጁ አለበት መባሉን የኡጋንዳ መንግሥት ቃል አቀባይ አስተባብለዋል።

"በተቃዋሚዎች ቤት ላይ የሚደርስ ፍንዳታ መንግሥትን ለመወንጀል ሆን ተብሎ የሚደረግ ሤራ ነው" ሲሉ ኦፍዎኖ ኦፖንዶ ለኒው ቪዥን ጋዜጣ ተናግረዋል።

ክያጉላንዪን የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ዕድሜ ጣሪያ እንዳይነሳ በመቃወሙ በየዕለቱ የሞት ዛቻ እየደረሰው መሆኑን አስታውቋል።

የሚደርስበት ዛቻ ግን እንደማያስፈራው ተናግሯል።

Image copyright Allan Ssewanyana Bwino

"በጥቃቱ ማንም አልተጎዳም። ግን በምን ዓይነት ሃገር እየኖርን ነው?" ሲል ጥያቄውን በፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።

ባለፈው ሳምንትም በሌላኛው ተቃዋሚ እና የፓርላማ አባል ሞሰስ ካሲባንቴ ቤት ላይ ጥቃት ተፈጽሞ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቪኒ ለ2021 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩ የማያደርጋቸውንና የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዕድሜ ጣሪያን በ75 የሚገድበውን ህግ ለመቀየር የሃገሪቱ ፓርላማ አባላት በከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት የኡጋንዳ ፓርላማ አባላት እስከ ድብድበ መዳረሳቸው ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች