ኤም ኤች 370 ጠፍቶ መቅረቱ ማይታሰብ ነው ሲል አንድ ሪፖርት ገለጸ

A message says: "MH370 we miss you" Image copyright AFP/Getty
አጭር የምስል መግለጫ ኤም ኤች 370 እ.አ.አ በ2014 ነበር 239 ሠዎችን ጭኖ ነበር የጠፋው

ንብረትነቱ የማሌዥያ አየር መንገድ የሆነው ኤም ኤች 370 አውሮፕላን ጠፍቶ መቅረቱን "የማይታሰብ" ሲሉ የአውስትራሊያ መርማሪዎች የመጨረሻ ነው ባሉት ሪፖርታቸው ይፋ አደረጉ።

ኤም ኤች 370 እ.አ.አ በ2014 ነበር፤ 239 ሠዎችን አሳፍሮ ከቤጂንግ ወደ ኳላላምፑር ሲያቀና የጠፋው።

ማሌዥያና ቻይናን ጨምሮ በትብብር ሲካሄድ የቆው ፍለጋም ከ1046 ቀናት በኋላ በይፋ ቆሟል።

የአውስትራሊያ መርማሪዎች አውሮፕላኑ ባለመገኘቱ "ክፉኛ ማዘናቸውን" አስታውቀዋል።

"በቀን 10 ሚሊዮን ሠዎች በአውሮፕላን በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ትልቅ የንግድ አውሮፕላን ከነመንገደኞቹ ጠፍቶ መቅረቱ የማይታሰብ እና በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ነው" ሲል የአውስትራሊያ የትራንስፖርት ደኅንነት ቢሮ አስታውቋል።

"በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳትፎ የተደረገው ትልቅ የማፈላለግ ሥራም ውጤት አላመጣም" ብሏል።

Image copyright AFP/Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎች ፍለጋው እንዲጀመር እየጠየቁ ነው

የመጨረሻ ነው የተባለለት ሪፖርት እንዳስታወቀው አውሮፕላኑ ቀድሞ ከተገመተበት ቦታ በሰሜን አቅጣጫ ነው የጠፋው።

ቦይንግ 777 የሆነውን ይህን አውሮፕላን ለመፈለግ የተደረገው እንቅስቃሴ በአየር ትራንስፖርት ታሪክ ውስጥ ትልቁ ነው ተብሎለታል።

ለ52 ቀናት በምድር ላይ ከተደረገ ፍለጋ በኋላ 120 ሺህ ስኩዌር ኪሎሜትር የሚሸፍን የውሃ አካል ላይም ፍለጋው ተጠናክሮ ቀጥሎ ነበር።

በ2015 እና 2016 የኤም ኤች 370 ስብርባሪ ነው የተባለላቸው የአውሮፕላን አካላት በተለያዩ ቦታዎች ተገኝተው ነበር።

የአውስትራሊያ መንግሥት ፍለጋው በድጋሚ የሚጀመረው አውሮፕላኑ የጠፋበት ቦታ በአስተማማኝ መረጃ ሲታወቅ ነው ብሏል።

የማሌዥያ መንግሥት በአውሮፕላኑ መጥፋት ዙሪያ የሚያደርገውን ምርመራ አሁንም ቀጥሎበታል።