የካታሎንያ ህዝበ ውሳኔ፡ የግዛቲቱ ነጻ ሀገርነት 'በጥቂት ቀናት ውስጥ'ይታወጃል

ካርለስ ፑይጅዲሞንት

ካታሎንያ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከስፔን ተነጥላ ነጻ ሀገርነቷን እንደምታውጅ የራስ ገዝ አስተዳደሩ መሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ካርለስ ፑይጅዲሞንት ከእሁዱ ህዝበ ውሳኔ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ''በዚህ ሳምንት መጨረሻ አሊያም በቀጣዩ ሳምንት መጀመሪያ'' መንግስታቸው እርምጃውን እንደሚወስድ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የስፔኑ ንጉሥ ፊሊፕ ስድስተኛ የህዝበ ውሳኔው አስፈጻሚዎች 'ከህግ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል' ሲሉ ወቅሰዋል።

ንጉሡ ስፔን ያለችበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ ህዝባቸው በህብረት እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ካታሎናውያን የስፔን ፖሊስ 900 ሰዎች በተጎዱበት የምርጫው ወቅት የኃይል እርምጃ ወስዷል በሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
የስፔን ፖሊሶች የመራጮችን ፀጉር ይዘው ሲጎትቱ የሚያሳየው ምስል መነጋገሪያ ሆኗል።

በወቅቱ 33 የፖሊስ አባላትም እንደተጎዱ ነው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የዘገቡት።

የካታሎንያው ፕሬዝዳንት የስፔን መንግስት ጣልቃ ገብቶ ለመቆጣጠር ቢሞክርስ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ''ሁሉንም ነገር የሚቀይር ስህተት ይሆናል'' የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

Image copyright AFP/Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ንጉሥ ፊሊፕ በቴሌቪዥን መልእክታቸው ህዝባቸው በህብረት እንዲቆም ጠይቀዋል።

ንጉሡ የካታሎንያውያንን ህዝበ ውሳኔ ያስፈጸሙ መሪዎች ''የሀገሪቱን የህግ የበላይነት ዲሞክራሲያዊ መርሆዎች ጥሰዋል'' ሲሉ ተደምጠዋል።

''ሆኖም ስፔን ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ታልፋለች'' ባይ ናቸው።

ማዕከላዊው መንግስትም ህዝበ ውሳኔውን በህገወጥነት ፈርጆታል።

ንጉሡ ያላነሱት ጉዳይ

ንጉሡ በንግግራቸው ፖሊስ በመራጮች ላይ ሲያደርስ ስለነበረው ድብደባም ሆነ ከካታሎንያ መንግስት ጋር ስለመወያየት ያሉት ነገር የለም።

ለካታሎናውያን የነጻ ሃገርነት ፍላጎትም እውቅና ሊሰጡ አልፈለጉም።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በህዝበ ውሳኔው 2.2 ሚሊዯን ሰዎች ድምጽ ሰጥተዋል

በምትኩ የመንግስታቸውን አቋም ማሰማትን መርጠዋል።

ህዘብ ውሳኔውን በጽኑ እንደሚቃወምና ዲሞክራሲያዊ መቻቻል እንደሚሰፍንም 'ዋስትና' ሰጥተዋል።

አስተያየት ሰጪ ዜጎች ግን ንጉሡ ሁለቱን ወገኖች ወደ ውይይት የማምጣት እድላቸውን እንዳበላሹ ነው የገለጹት።

"ይህ ችግሩን አይፈታም ፤ በጉዳዩ ጣልቃ ይገባሉ ብዬም አልጠበቅኩም፤ ቢያንስ ከሁለት ቀናት በፊት ስለነበረው ግጭት መጥቀስ ነበረባቸው'' ብሏል አንድ ስፔናዊ።

ባለፈው እሁድ በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ድምጽ ከሰጡት 90 በመቶ የሚሆኑት የካታሎንያን ነጻ ሀገርነት ደግፈዋል።

"ካታሎንያ ከስፔን ተገንጥላ አገር የመሆን መብቷን አሸነፈች"

ነገር ግን እስካሁን ይፋዊ መረጃ አልወጣም።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ