የስፔን ፍርድ ቤት የካታሎንያ ፓርላማ የነጻነት እርምጃ ላይ እገዳ ጣለ

የካቶሎኒያ ነጻነት ደጋፊዎች Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ የካታሎንያ ነጻነት ደጋፊዎች ሰለማዊ ሰልፍ ቀጥሏል

የስፔን ፍርድ ቤት በመጪው ሰኞ ሊካሄድ የነበረ የካታሎንያ ፓርላማ ስብሰባ እንዳይካሄድ እገዳ ጥሏል።

እርምጃው ካታሎንያ ከስፔን ተገንጥላ ነጻ ሃገር የመሆኗን ሩጫ እንድታቆም ጫና ለማሳረፍ የተወሰደ ነው።

ፍርድ ቤቱ የካታሎንያን እርምጃ ''ህገመንግስቱን የጣሰ'' ብሎታል።

ከዚህ ቀደምም የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያኖ ራጆይ የካታሎንያን መንግስት አስጠንቅቀዋል።

የካታሎንያው መሪ ካርለስ ፑጅደሞን ደግሞ በቀጣዩ ሳምንት ነጻ ሀገርነቷን እንደምታውጅ አመላክተው ነበር።

ከካታሎንያ የነፃነት ጥያቄ ጀርባ

በእሁዱ ህዝበ ውሳኔ የተሳተፈው 2.2 ሚሊዮን ህዝብ ድምጽ መስጠት ከሚችለው ህዝብ 42 በመቶውን ይሸፍናል።

ከነዚህም 90 በመቶ የሚሆኑት ነጻ ሃገር መሆኗን ደግፈዋል።

እስካሁን ግን የመጨረሻውን ውጤት በይፋ አልተገለጸም።

በምርጫው አፈጻጸም ላይ የተስተዋሉ ችግሮች እንደነበሩ የሚያነሱም አሉ።

በምርጫ ጣቢያዎች ፖሊስ የምርጫ ኮሮጆዎችን በመቀማትና መራጮችን በመበተን ህዝበ ውሳኔውን ለማስቆም ሲሞክር ግጭቶች ተቀስቅሰው ነበር።

ይህን ተከትሎም ባለፈው ሃሙስ ሳባዴል የተሰኘው ግዙፍ ባንክ በህግ የተመዘገበ መቀመጫውን ከባርሴሎና ወደ ደቡብ መስራቋ አሊካንቴ አዘዋውሯል።

በተመሳሳይም ኬይክሳ የተሰኘው ሌላ ባንክም ተመሳሳይ እርመጃ ለመውሰድ ማቀዱ እየተነገረ ነው።

ይህ ደግሞ ባንኮቹ በዩሮ ቀጠና ውስጥ እንዲቆዩና በአውሮፓ ብሄራዊ ባንክ አስተዳደር ስር እንዲቆዩ ያደርጋል።

የባርሴሎናው እግርኳስ ክለብ አምበል አንድሬስ ኢኒሽታ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት እንዲካሄድ ተማጽኗል።

'ለሁላችንም ስትሉ አድርጉት፤ በሰላም መኖር ይገባናል'' ብሏልየ 33 ዓመቱ ተጫዋች በፌስቡክ ገጹ ላይ።

ተያያዥ ርዕሶች