ካለሁበት 4፡ የሰው ሃገር የሰው ነው፤ ያለሁበት መጠለያ ጣቢያ እስር ቤት ውስጥ እንደ መኖር ነው

ካኩማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ
አጭር የምስል መግለጫ ካኩማ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በረሃማ በሆነው ሰሜናዊ ኬንያ ይገኛል።

ስደት ህይወቴን ያትርፍልኝ እንጂ የስደተኝነት ኑሮ እጅግ መራራ ነው።

ዱሬሶ ሞሲሳ እባላለሁ። ኬንያ ቱርካና ግዛት (ካውንቲ) ውስጥ ካኩማ በሚባል የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ነው የምኖረው።

በዚህ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከተለያዩ ሃገራት የመጡ ከ200 ሺህ በላይ ስደተኞች ይኖራሉ።

በካኩማ መኖር እጅግ ከባድ ነው። አካባቢው በረሃማ ስለሆነ ሙቀቱ በአማካይ 30 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል። ወባን ጨምሮ በካኩማ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋለጠናል። ከዚህም በላይ በካኩማ እንደ እባብ እና እፉኚት ያሉ መርዛማ ተሳቢ እንስሳት በብዛት ይገኛሉ። በእነዚህ መርዛማ ተሳቢ እንስሳት እየተነደፉ ብዙ የሚሞቱ ሰዎች አሉ።

ወደዚህ የመጣሁት የኢትዮጵያን መንግሥት ሽሽት ነው። የኦነግ ደጋፊ ነህ ተብዬ 8 ዓመታትን በእስር ከተንገላታሁ በኋላ ተለቀኩኝ። ከእስር ቤት ከወጣሁም በኋላ ይከታተሉኝ ነበር። ክትትላቸው እረፍት ነሳኝ። በሄድኩበት ይከተሉኛል።

ከዛም ህይወቴን ለማዳን ስል ሃገሬን ጥዬ ለመሰደድ ወሰንኩ። ከሃገሬ በቀጥታ ወደ ኬንያ ነበር የመጣሁት። ከሃገሬ ከወጣው 11 ዓመታት አለፉ። በስደት ለኑሮ በማይመቸው ካኩማ 11 ዓመታትን ማሳለፍ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው።

ካኩማ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ በውስጡ የተለያዩ መንደሮች አሉት። ካኩማ 1፣ ካኩማ 2 እና 3 በመባል ይታወቃሉ። እኔ የምኖረው ካኩማ 1 ውስጥ ነው።

በካኩማ 1 ውስጥ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የመጡ ስደተኞች በብዛት ይኖራሉ። እኛ የምንኖርበት መንደር ከሌሎች በተሻለ መልኩ ዛፎች አሉት። ከኛ በፊት የነበሩ ስደተኞች የተከሏቸው ናቸው።

ዛፎቹ የአካባቢውን ሙቀት ጋብ ስለሚያደርጉልን ሁላችንም በተቻለን መጠን ለመጠጥ ከሚታደለው ውሃ በመቀነስ ዛፎቹን በማጠጣት እንከባከባለን።

አጭር የምስል መግለጫ በካኩማ የስደተኞች ጣቢያ ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ።

ከሃገር ቤት ከሁሉ በላይ የሚናፍቁኝ ቤተሰቦቼ ናቸው። ለዓመታት ከደረሰብኝ ስቃይ በላይ ከቤተሰቤ ሳልፈልግ መለየቴ ሁሌም ያሳዝነኛል።

እንደ ኢትዮጵያ እስር ቤት የሚደርስብኝ ስቃይ እና ድብደባ የለም አንጂ በዚህም መንቀሳቀስ ስለማልችል እስር ቤት እንዳለሁ ነው የሚሰማኝ።

በህይወቴ መልካም ነገር ተፈጠረ የምለው ከሶስት ዓመት በፊት የሴት ልጅ አባት መሆኔ ነው። የልጄን ዓይን ስመለከት ደስታ እና ሠላም ይሰማኛል። በህይወቴ የገጠመኝን ችግር እና ስቃይ የምረሳው ልጄን ሳስባት ነው።

ወደፊትም የተሻለ ህይወት ሊገጥመኝ እንደሚችል አስባለሁ።

በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ባለ ድርጅት ውስጥ የተለያዩ ስራዎችን በመስራት በማገኝው አነስተኛ ገንዘብ ልጄን አሳድጋለሁ።

ብዙ እንደመቆየቴ መጠን የኬንያን ምግብ በደንብ ተላምጄዋለሁ። ኡጋሊ በጎመን ምርጫዬ ነው።

እንደው ቢቻል እና በአንድ ተዓምር አምቦ ካሉት ቤተሰቦቼ መሃል ከልጄ ጋር እራሴን ባገኘው ደስታዬ ወደር አይኖረውም ነበር።

ለጫሊ ነጋሳ እንደነገረው

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦

ካለሁበት 5፡'ኑሮዬን ቶሮንቶ ያደረግኩት በአጋጣሚ ነበር'

ካለሁበት 6 ''ከሀገር ቤት የስደት ኑሮዬ ይሻለኛል''

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ