ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ ‘የ2017 የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ዲዛይነር’ ሆነች

ኮከብ ሽልማቷን ይዛ Image copyright koki designs

ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የኬንያ የፋሽን ሽልማት 'የ2017 የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ዲዛይነር' ሆና ተመርጣለች።

ውድድሩ ለወራት በድረ ገጽ ድምጽ ሲሰጥበት ቆይቶ የዘርፉ ባለሙያዎች ሙያዊ ዳኝነት ታክሎበት ፍጻሜውን አግኝቷል።

የሽልማቱ አንዱ ዘርፍ በሆነው 'የምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ዲዛይነር' ውድድር ደግሞ በናይሮቢ የምትኖረው ኢትዮጵያዊቷ ኮከብ ዘመድ አሸናፊ ሆናለች።

ባለፈው ቅዳሜ በናይሮቢ በተካሄደው የውድድሩ ማሳረጊያ መርሃ ግብር ኮከብ የፋሽን ትርዒት አቅርባ ሽልማቷንም ከአዘጋጆቹ ተቀብላለች።

ኮከብ ለዚህ ሽልማት ከኬንያ፣ ከሩዋንዳና ከታንዛኒያ እጩ ከሆኑ አምስት ሌሎች ዲዛይነሮች ጋር ተፎካከራለች።

የሽልማቱ አላማ በኢንዱስትሪው የራሳቸውን አዲስ እይታ ተጠቅመው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ዲዛይነሮች ክብር መስጠት እንደሆነ በአዘጋጆቹ ድረገጽ ላይ ሰፍሯል።

የመገምገሚያ መስፈርቶቹ ደግሞ አዳዲስ ፈጠራ ፣ ጥሩ የዲዛይን አጨራረስ፣ የግል ምልከታና ለሌሎች አርአያ መሆናቸውን ይጨምራል።

ኮከብ ከአውሮፓውያኑ 2009 ጀምሮ ባቋቋመችው ኮኪ ዲዛይንስ የኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አልባሳትን እያዋሃደች የአፍሪካን ባህል በዲዛይኖቿ ታስተሳስራለች።

በቅኝ ከተገዙባት ብሪታኒያ የመጣው የኬንያ ዳኞች አለባበስ የነጻነት ተምሳሌት በሆነ ካባ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀየረው በኮኪ ዲዛይንስ ነው።

Image copyright Adele Dejack
አጭር የምስል መግለጫ በውድድሩ በ2017 በፋሽን ኢንዱስትሪ በ13 ዘርፎች ስኬት ያስመዘገቡ ተሸልመዋል

የኬንያ ዳኞችን አለባበስ የቀየረች ኢትዮጵያዊት

ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ልብስ በተጨማሪ ደግሞ ሌሎች አፍሪካውያን የሚቀምሙላትን ባህላዊና ዘመናዊ ልብሶች ታዘጋጃለች።

ለሴቶች ፣ ለወንዶችና ለልጆች ለልዩ ዝግጅት፣ ለሥራ ቦታና ለበዓላት የሚሆኑ ንድፎችን ቀርጻ በተለያዩ የፋሽን ትርዒቶች ላይ ታሳያለች፤ ለገበያም ታቀርባለች።

የኢትዮጵያን ባህላዊ የሸማ ጨርቆችና ጥለቶችን ከሌላ ዘመናዊ ጨርቅ ጋራ እያዋሃደች ለየእለት ሥራ ምቹ በሚሆን መልኩ ስታዘጋጅ ቆይታለች።

በነዚህ ሁሉ ሥራዎቿ ታዲያ የምትከተለው መርህ የፋሽን ሚና 'የቀድሞውን ባህላዊ አልባሳት ከዘመኑ ጋር እያዋሃዱ የማሳደግ እንጂ እነርሱን ጥሎ በአዳዲሶች የመተካት ሊሆን አይገባም' የሚል ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ