የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እህቱን ለፖሊት ቢሮ ሾመ

ከወንድሟ አካባቢ የማትጠፋው ኪም ዮ ጆንግ ከጀርባ ያለችው ናት Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ከወንድሟ አካባቢ የማትጠፋው ኪም ዮ ጆንግ ከጀርባ ያለችው ናት

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የእህቱን ስልጣን በማሳደግ፤ በአገሪቷ ላይ ከፍተኛ የመወሰን ሃላፊነት ወዳለው ፖሊት ቢሮ አባል እንድትሆን ሾሟታል።

ኪም ዮ ጆንግ የ ቀድሞው መሪ ኪም ጆንግ ኢል የመጨረሻ ልጅ ስትሆን አሁን ያለውንም የስልጣን ቦታም የተቆጣጠረችው የሰራተኞች ፓርቲን በመወከል የፖሊት ቢሮ አባል የነበረችውን አክስቷን በመተካት ነው። የ 30 አመት ዕድሜ ያላት ኪም ዮ ጆንግ ወደ ከፍተኛ ስልጣን ቦታ መቆናጠጥ የጀመረችው ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር።

አጠቃላይ ቤተሰቡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ማግስት አንስቶ ሰሜን ኮሪያን በመምራት ላይ ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎች ከወንድሟ ጋር በአደባባይ የምትታየው ኪም ዮ ጆንግ፤ በአደባባይ ላይ ላለውም እይታ ከፍተኛ ተፅዕኖን የፈጠረች ሲሆን የፕሮፓጋንዳ ክፍልን እንዲሁም ቀውሶች በሚፈጠሩበትም ጊዜ የሚመራው ክፍል ምክትል ሃላፊ ነች። ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋርግንኙነት አላት በሚል በአሜሪካ መንግሥት በጥቁር መዝገብ ከሰፈሩት ውስጥ አንዷ ናት። ይህ ሹመት የተነገረው ቅዳሜ በነበረው የፓርቲው ስብሰባ ላይ ሲሆን በዚህም ስብሰባ ላይ ከፍተኛ የሚባሉ የባለስልጣናት ሽግሽግ ተደርጓል።

በባለፈው ዓመት በመሪው ፓርቲ ኮንግረስ ቁልፍ የሚባል ስልጣን ሲሰጣት በሃገሪቷም ላይ ከፍተኛ ስልጣን እንደምትቆናጠጥ ተጠብቋል።

ኪም ዮ ጆንግ ማናት?

ቅዳሜ ዕለት ሌላኛው ሹመት የተሰጣቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዮንግ ሆ ሲሆኑ፤ ባለፈው ወር የአሜሪካ ፕሬዚዳንትን ዶናልድ ትራምፕን በተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ "መጥፎው ፕሬዚዳንት" በሚል ንግግር መወረፋቸው ይታወሳል። በፖሊት ቢሮው ውስጥ በሙሉ ድምፅ የመሳተፍንም ሹመት አግኝቷል።

በኒዉክሌር መሳሪያ ላይ ጠንካራ አቋም ያለው ኪም አሁንም ግልፅ ያደረገው ምንም አይነት ማዕቀብ ይሁን ማስፈራራት ከእቅዳቸው እንደማያሰናክላቸው ነው። ይህ አስተያያየት የተሰጠው ትራምፕ ከሰዓታት በፊት በትዊተር ገፃቸው " ከፒዮንግያንግ ጋር ለመደራደር አንድ ነገር ብቻ ነው የሚሰራው'' ያሉ ሲሆን ከዓመታት ንግግርም በኋላም ውጤቶች ማምጣት አልተቻለም ብለዋል።