የቱርክና የአሜሪካ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል

የቱርክና የአሜሪካ ባንዲራ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የቱርክና የአሜሪካ ባንዲራ

ቱርክና አሜሪካ ለዜጎቻቸው የሚሰጡትን ቪዛ አገልግሎት በማቋረጥ ዲፕሎማቲክ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።

ዋሽንግተን የሚገኘው የቱርክ ኤምባሲ እንዳለው የአሜሪካ መንግሥት የኤምባሲውን ሰራተኞች ደህንነት ለማስጠበቅ የገባውን ቃል በተመለከተ መልሰን መመርመር አለብን ብሏል።

አንካራ ቱርክ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲም ተመሳሳይ መግለጫ ቀደም ብሎ ሰጥቶ ነበር።

ውዝግቡ ተጀመረው ባለፈው ዓመት ተሞክሮ ለከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት ተጠያቂ ከሆኑት የሃይማኖት መሪ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ የተጠረጠረ በኢስታምቡል የአሜሪካ ቆንስላ ሰራተኛ ከተያዘ በኋላ ነው።

ዋሽንግተን እርምጃውን መሰረተ ቢስና የሃገራቱን ሁለትዮሽ ግንኙነት የሚጎዳ ስትል አውግዛዋለች።

የቱርክ መንግሥት ዜን ወኪል የሆነው አናዱሉ እንደዘገበው በቁጥጥር ስር የዋለው የአሜሪካ ቆንስላ ተቀጣሪ የቱርክ ዜግነት ያለው ነው።

የአሜሪካ መንግሥት ለሰራተኞቹ የሚያደርገውን ጥበቃ አስኪመረምሩ ድረስ፤ ወደ ቱርክ ኤምባሲና ቆንስላ የሚመጡ የባለጉዳዮችን ቁጥር ለመቀነስ ለአሜሪካ ዜጎች የሚሰጠውን የቪዛ አገልግሎት ማቋረጡን ኤምባሲው ገልጿል።

የቱርክ መግለጫ ቀደም ብሎ ከወጣው የአሜሪካ መግለጫ ጋር የሀገራቱ ስም ከመቀየሩ በቀር አንድ አይነት ነው።

የአሜሪካ ኤምባሲም ከቱርክ የሚሰጡ የአሜሪካ የቪዛ አገልግሎቶች በሙሉ ተቋርተዋል ሲል አሳውቋል።

ቱርክ ከዓመት በፊት ተሞክሮ በነበረው መፈንቅለ መንግሥት ውስጥ እጃቸው አለበት የሚባሉትን በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑት የሃይማኖት መሪ ፋቱላህ ጉለን ተላልፈው እንዲሰጧት አጥብቃ ዋሽንግተንን ስትጠይቅ ቆይታለች።

በወታደራዊ መኮንኖች የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥትን ተከትሎ 40 ሺህ ሰዎች የተያዙ ሲሆን፤ 120 ሺህ የሚደርሱት ደግሞ ከሥራቸው ታግደዋል ወይም ተባረዋል።