ኤርኔስቶ ጉቬራ፡ አባቴ ኩባን በሞተር ሳይክል እንዳስጎበኝ እንዴት መነሻ ሆነኝ?

የደፈጣ ተዋጊው ኤርኔስቶ "ቼ" ጉቬራ መስከረም 28/1960 ነበር ቦሊቪያ ውስጥ የተገደለው። ከ50 ዓመታት በኋላ የቢቢሲው ዊል ግራንት ወደ ኩባ አቅንቶ ከልጁ ጋር በአባቱ ጥላ ስር ስለመኖር እና ሌሎችም ጉዳዮች ጠይቆታል።
በቤተሰቡ መካከል መመሳሰል ይታያል።
በጺም የተሞላ ፊት፥ አፍንጫ መመሳሰሉ ቀጥሎም ረዥም ሲጋራ በጣቶች መሃል ይታያል።
ልጁ ከአካላዊው መመሳሰል በተጨማሪ ከላቲን አሜሪካው ታዋቂ አብዮተኛ ኤርኔስቶ "ቼ" ጉቬራ ጋር ሌላም የሚጋሩት ነገር አላቸው - የሞተር ሳይክል ፍቅር።
ለሞተር ሳይክል ተመሳሳይ ፍቅር ቢኖራቸውም ትንሹ ጉቬራ ግን የህይወቱን አቅጣጫ ወደ ቱሪዝም አዙሯል።
በሞተር ሳይክል የማስጎብኘት ሥራ የሚያከናውን ላ ፖዴሮሳ ቱርስ የተባለ ድርጅት አቋቁሟል። ድርጅቱ ከቼ ጋር የሚገናኘው በስሙ ብቻ ነው። ድርጅቱ ስያሜውን ያገኘው ቼ ይጠቀምባት ከነበረው ላ ፖዴሮሳ ከተሰኘችው ሞተር ሳይክል ነው።
ላ ፖዴሮሳ ቱርስ በሠው ሃገር የሚንቀሳቀስ የግል ድርጅት ሲሆን መንግሥታዊ ከሆኑ ብዙ የኩባ ኩባያዎች ጋርም ይሠራል። ዕድሉ የተፈጠረው ፕሬዝዳንት ራውል ካስትሮ እ.አ.አ በ2010 ከቀየሩት ህግ በኋላ ነው።
በምዕራብ አቅጣጫ በሲጋራ ምርቷ ወደ ምትታወቀውን ፒናር ዴል ሪዮን ለመጎብኘት በቅርቡ በተዘጋጀ ጉዞ ላይ ነበር ያገኝሁት።
በሞተር ሳይክል ደሴቷን መጎብኘት እየተለመደ መጥቷል። በጉብኝቱ ላይ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች ተሳታፊዎች ነበሩ። አሜሪካ፣ ቻይና፣ እንግሊዝ፣ አርጀንቲናን ጨምሮ ከተለያዩ ሃገራት የተወጣጡ ሞተረኞችም ተሳታፊ ሆነዋል።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ኩባን የጎበኙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ያደገ ሲሆን የላ ፖዴሮሳ ቱርስ ገበያም የተጧጧፈ ነበር።
ኤርኔስቶ በተለይም በሚያሚ የሚኖሩ ተቺዎች እንዳሉት ያውቃል። ብዙ ጊዜም ለማርኪሲስት እንደ ምልክት ከሚታይ ሰው ተወልዶ ጉቬራ ግን በካፒታሊዝም ስራ ላይ ተሰማርቷል እየተባለ ይገለጻል።
ይህ ክስ ግን ምንም አያስጨንቀውም።
"ይህ ከካፒታሊዝምም ሆነ ከሶሻሊዝም ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም" ሲል ይከራከራል።
"ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ አይደለም። እንደእኔ ሃገሬን የሚረዳ ጥሩ ስራ በመሥራት ላይ እንገኛለን" ሲል ይገልጻል።
እጅግ ታዋቂ ከሆነ አባት መወለድ ወይም ያለአባት ማደግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም ሲል ያስረዳል። ቼ ጉቬራ ቦሊቪያ ውስጥ መስከረም 28/1960 ሲገደል ኤርኔስቶ ገና የሁለት ዓመት ህጻን ነበር።
"አንድ አንድ ጊዜ ትምህርት ቤት ውስጥ 'ኤርኔስቶ ጉቬራ' በሚል ልትለይ ትችላለህ። ብዙ ጊዜ ግን ራስህን በሆንከው 'ኤርኔስቶ ጉቬራ ማርች' በሚለው ነው በደንብ የምትታወቀው። የእናትህም የአባትህም ልጅ ሆንክ ማለት ነው" ይላል።
በመላው ዓለም እንደምልክት የሚታየው አባቱ ያለው አድናቆት ምንም አይነት መቀዛቀዝ ባይታይበትም ትንሹ ኤርኔስቶ ማስገንዘብ የሚፈልገው ጉዳይ አለ።
"የሚወዱኝ ሰዎች በእኔነቴ ብቻ ይውደዱኝ። ጉቬራ የሚለውን ስም ምክንያት በማድረግ እንዲወዱኝ አልፈልግም" ሲል ይገልጻል።