የቱኒዚያ የጤና ሚንስትር ስሊም ቻኬር ከበጎ አድራጎት ሩጫ በኋላ ህይወታቸው አለፈ

ሳሊም ቻኬርን የሚያሳይ ምስል Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ሳሊም ቻኬር የጤና ሚንስትር ሆነው የተሾሙት ከወር በፊት ነበር

ካንሰርን ለመዋጋት በተዘጋጀ የበጎ አድራጎት የማራቶን ሩጫ ላይ የተሳተፉት የቱኒዚያው የጤና ሚንስትር በልብ ድካም ምክንያት ህይወታቸው አለፈ።

የ56 ዓመቱ ስሊም ቻኬር 500 ሜትር ያህል ከሮጡ በኋላ ህመም ተሰምቷቸው በወታደራዊ ሆስፒታል ህክምና ቢከታተሉም ህይወታቸው ማለፉ ይፋ ተደርጓል።

ሳሊምን "ወንድሜና የስራ ባልደረባዬ" ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዩሱፍ ቻሄድ፣ ሳሊም ተደናቂ እና ሠብዓዊ ምግባር ላይ ሲሳተፍ ህይወቱ አልፏል ብለዋል።

ለህጻናት የካንሠር ህሙማን ክሊኒክ ለመገንባት የተዘጋጀው የማራቶን ውድድር በናቤዩል ከተማ ባለፈው እሁድ ነበር የተካሄደው።

ሳሊም ባለፈው ወር በቱኒዚያ የተካሄደውን የካቢኔ ለውጥ ተከትሎ ነበር ሚንስትር ሆነው የተሾሙት።

ሚንስትሩ ቀደም ሲል የባንክ ሠራተኛ ሆነው ሰርተዋል። ለረዥም ጊዜ ሃገሪቱን የመሩት ዛይን ኣል-አብዲን ቤን እ.አ.አ በ2011 ከስልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ ሳሊም በፋይናንስ፣ ስፖርትና ወጣቶች ሚንስትር ውስጥም አገለግለዋል።


የልብ ድካም ምልክቶች

  • የደረት ህመም-በመሐል ደረት አካባቢ የሚኖር ግፊት፣ ውጥረት ወይም ጭንቀት
  • በተለያዩ ሠውነት ክፍሎች ላይ ያለ ህመም- ከደረት አካባቢ የሚነሳ ህመም በግራ እና በቀኝ እጅ፣ መንጋጋ፣ አንገት፣ ጀርባ እና ሆድ ድረስ ሚሄድ ይመስላል። ብዙ ጊዜ ግራ እጅ ላይ ያጋጥማል።
  • ጨንቅላት የመቅለል ስሜትና እና መደንዘዝ
  • ማላብ
  • ለመተንፈስ መቸገር
  • ማቅለሽለሽ ወይም ምግብ አለመርጋት
  • በአጠቃላይ አለመረጋጋት
  • ማሳልና በሃይል መተንፈስ

የደረት ላይ ህመሙ ብዙ ጊዜ ከባድ ቢሆንም አንድ አንድ ሰዎች እንደምግብ አለመፈጨት የሚመስል ቀላል ህመም ብቻ ይሰማቸዋል።

በተለይ ደግሞ በሴቶች፥ በዕድሜ በገፉ ሰዎችና በስኳር ህሙማን ዘንድ ምንም የደረት ህመም ላይኖር ይችላል።

ምንጭ: NHS

ተያያዥ ርዕሶች