የተባበሩት መንግሥታት አራት መርከቦች የሰሜን ኮሪያን ማዕቀብ በመጣስ አግዷል

የታገዱት መርከቦች Image copyright AFP

የተባበሩት መንግሥታት አራት መርከቦችን የትኛውንም ዓለም አቀፍ ወደቦች እንዳይጎበኙ አግዷል። ይሄም እገዳ የመጣው በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ስለጣሱ ነው።

ሂዩግ ግሪፍዝስ በተባበሩት መንግሥታት የሰሜን ኮሪያን ማዕቀብ ቡድን አስተባባሪ ሲሆን ይሄንንም እርምጃ ያልተጠበቀ ብለውታል።

መርከቦቹም ፔትሬል 8፣ ሃዎ ፋን 6፣ ቶንግ ሳን 2 እንዲሁም ጂ ሸን የሚባሉ ናቸው።

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ፤ በቅርቡ ሃገሪቱ ባደረገችው በስድስተኛና ትልቁ የኒውክሊየር ሙከራዋ ምክንያት ባለፈው ዘርፎችን እንዲያካትት ባለፈው ወር መወሰኑ ይታወሳል።

ይህ እገዳ የታወጀውም ሰኞ በነበረው የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ ነው።

ሂዩግ ግሪፍዝስ እንዳሉት ሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ከማጥበቅ ጋር ተያይዞ ከተደረገው ስብሰባ በኋላ፤ መርከቦቹ የተከለከሉ ዕቃዎችን ሲያጓጉዙ ተገኝተዋልም ብለዋል።

ጨምረውም እንደተናገሩት ይህ እገዳ የተተገበረው ከመስከረም 25 ጀምሮ ሲሆን ንብረት እንዳይንቀሳቀስ ወይም የጉዞ እገዳን ያካተተ አልነበረም ብለዋል።

ማሪን ትራፊክ የተባለው ድረገፅ እንዳሰፈረው ፔትሬል 8 ኮሞሮስ፣ ሃዎ ፋን 6 በሴይንት ኪትስና ኔቪስ፣ ቶንግ ሳን 2 በሰሜን ኮሪያ ተመዘገቡ ሲሆኑ ጂ ሸን የተመዘገበችበት አገር አልተጠቀሰም።

ወደ ውጭ የመላክ እገዳ

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የተባበሩት መንግሥታት ሰሜን ኮሪያ የድንጋይ ከሰል፣ የባህር ውስጥ ምግቦች እንዲሁም የብረት ማዕድን ወደ ውጭ እንዳትልክ ውሳኔ አስተላልፏል።

ማዕቀቡ ባለፈው ወር እንዲሰፋ የተደረገ ሲሆን የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን ወደ ውጭ እንዳትልክ እንዲሁም ጊዜያዊ ሰራተኞች በሌላ አገር እንዳይሰሩና የምታስገባው የነዳጅ ዘይት ምርት የተወሰነ እንዲሆን ወስኗል።

የማዕቀቡ እንዲጠብቅ የተደረገው ሰሜን ኮሪያን ለስድስተኛ ጊዜ የኒውክሊየር ሙከራ በማድረጓና ወደ ጃፓን ሁለት ሚሳይሎችን መተኮሷን ተከትሎ ነው።

የሰሜን ኮሪያ ዋና የኢኮኖሚ አጋር የሆነችው ቻይና ይሄንን እርምጃ ከራሺያ ጋር በመሆን ፈርመዋል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱ ሃገራት ሰሜን ኮሪያ ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ይወሰድ ሲባል፤ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው የቀረበውን ሃሳብ ውድቅ ያደርጉት እንደነበር የሚታወስ ነው።

ሰሜን ኮሪያ ወደ ቻይና የምትልካቸው የብረት ማዕድን፣ የድንጋይ ከሰል እንዲሁም ሌሎች ያልተጣሩ ማዕድናት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝባቸው ናቸው።

ሰሜን ኮሪያ ወደውጭ የምትልካቸው ዕቃዎች ዋጋ 3 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሲሆን ማዕቀቡም 1 ቢሊየን ዶላር የሚሆነውን ሊያሳጣት ይችላል።

በተደጋጋሚ የተጣሉባት ማዕቀቦች ሰሜን ኮሪያ የምታካሂደውን የኒውክሊየር እንዲሁም የሚሳይል ግምባታ ፕሮግራሟን እንድታቆም ሳያደርጓት ቆይተዋል።