100 ሴቶች፡ ሴት መሪዎች የሌሎች ሴቶችን ህይወት ይቀይራሉ?

Hillary Clinton supporters at the Javits Center Image copyright KENA BETANCUR
አጭር የምስል መግለጫ ጃቪትስ ማዕከል

"የመስታወቱን ስንጥቅ ሙሉ ለሙሉ ደፍነናል ብዬ አላምንም...በቀጣይ ፕሬዝዳንት ልሆን እችላለሁ። ይህን ከሚመለከቱ ሴቶች መካከል ደግሞ አንዷ ቀጣይዋ ፕሬዝዳንት ልትሆን ትችላለች።" ሒላሪ ክሊንተን ይህንን የገለጹት እ.አ.አ ሰኔ 2016 የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ በሆኑበት ወቅት ነው።

ሒላሪ ህልማቸውን ባያሳኩም በአጋጣሚ ግን ለምርጫው ዕለት የመረጡት ቦታ ከንግግራቸው ጋር ተመሳሳይ ሆኗል።

ጃቪትስ ማዕከል በኒውዮርክ ከተማ ከሚገኙ ማዕከላት ትልቁን የመስታወት ጣራ ባለቤት እንደሆነ ይገመታል። ሒላሪ የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው ቢሆኑ ኖሮ ምርጡ ቦታቸው ይሆን ነበር።

ሒላሪ ምርጫውን ማሸነፍ ባይችሉም ባለፉት አስር ዓመታት ወደ ስልጣን የመጡ ሴቶች ቁጥር በሁለት እጥፍ አድጓል።

በአሁኑ ወቅት 15 ሴቶች በስልጣን ላይ የሚገኙ ሲሆን ስምንቱ የሃገራቸው መሪ በመሆን እያገለገሉ ነው ይላል የፔው ሪሰርች ማዕከል ጥናት።

ሆኖም አሁንም ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሃገራት መካከል፤ ከአስር በመቶ በታች በሚሆኑት ብቻ ነው ሴቶች በመሪነት ቦታ የሚገኙት።

እነዚህ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሴት መሪዎች መስናክሎችን ጥሰው አልፈዋል። ግን ሌሎች በሃገራቸው የሚገኙ ሴቶችን ወደራሳቸው አምጥተዋል? በህንድ ክልላዊ አስተዳደር ውስጥ ተግባራዊ የሆነው የፖለቲካ ዘዴ ለዚህ ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል።

ከ1993 ጀምሮ ከሶስት የህንድ ገጠራማ አካባቢዎች መካከል አንዱ በዕጣ ተመርጦ የአስተዳዳሪነትን ሚናው ለሴቶች ይሰጣል። ይህም ለማህበራዊ ጥናት ትልቅ መሠረት ሆኗል።

በ2012 በሺዎች በሚቆጠሩ ልጃገረዶችና ወላጆቻቸው ላይ በተደረገ ጥናት መሠረት ሴት መሪዎች መኖራቸው ለወጣት ሴቶች መነሳሳትን እንደሚፈጥር ለማወቅ ተችሏል።

Image copyright Sean Gallup
አጭር የምስል መግለጫ ሒላሪ ክሊንተን እና አንጌላ ሜርኬል

ወላጆች የልጆቻቸውን የትምህርት፣ ዕድሜ እና የስራ ዘርፍ መሠረት በማድረግ በወንድ ልጆቻቸው ስኬታማነት ላይ ይበልጥ እምነት አላቸው።

ይሁን እንጂ አንድ መንደር በሁለት የምርጫ ጊዜ ሴት መሪዎችን ሲያገኝ፤ ሴት መሪ ካላገኙት አንጻር ወላጆች በወንዶች እና በሴት ልጆቻቸው መካከል ያለው የስኬታማነት እምነት በ 25 በመቶ ተቀራርቧል።

ሴት መሪዎች ባለው ፖሊሲ የሴቶችንና የልጃገረዶችን ሁኔታ ለመቀየር ሰፊ ዕድል እንደሌላቸው ባለስልጣናት ተረድተዋል። ሆኖም በትምህርት እና ለሌሎች አርአያ በመሆን የሚፈጥረው መነሳሳት አዎንታዊ ሆኗል።

አንድ የስዊዝ ጥናት እንደሚያሳየው አርአያ የሆኑ ሰዎች በርቀትም ሆነውም የሴቶችን ህይወት መቀየር ይችላሉ።

ባለስልጣናት ሰው ያለበት የሚመስል ግን ማንም በሌለበት ቦታ ወንዶችንና ሴቶችን በአራት ቡድን ከፍለው ንግግር እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረበው ነበር።

የመጀመሪያው ቡድን አባል የጀርመኗን መራሄተ መንግሥት አንጌላ መርኬልን ሲያይ፤ ሁለተኛው በወቅቱ አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩትን ሒላሪ ክሊንተንን፤ ሶስተኛው ቡድን ቢል ክሊንተንን ሲያይ የመጨረሻው ቡድን ማንም በሌለበት ንግግር እንዲያደርግ ተደረገ።

ሴት ተናጋሪዎች ማንም ከሌለበት ወይም ከወንድ ፖለቲከኛ ይልቅ ውጤታማ ሴት ፖለቲከኛ ባለችበት ረዥም ሰዓት ወስደው ተናግረዋል። ብዙም በተናገሩ ቁጥርም ንግግራቸው አዎንታዊ እንደሆነ ያስባሉ።

"የእኩልነቱ ግብ የሴት ፖለቲከኞችን ቁጥር ማሳደግ ብቻ ሳይሆን በዚህ ምክንያት የሚመጣውን አዎንታዊ ስሜት ከፍ ማድረግ ነው" ሲሉ የሪፖርቱ ጸሐፊ ይገልጻሉ።

ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ማደጉ ከህይወት መሻሻል ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት መኖሩ ለዚህ መሳያ ይሆናል።

የጤና፣ የትምህርት፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካዊ ተሳትፎን ከግምት በማስገባት የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የሃገራትን ዓለም አቀፍ የስነ-ጾታ ልዩነት ደረጃ ይፋ ያደርጋል።

እ.አ.አ በ2016 ስነ-ጾታ ልዩነታቸው አጥብበዋል የተባሉት አይስላንድ፣ ፊንላንድ እና ኖርዌይ በፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉ ብዙ ሴቶች ካላቸውም መካከል ናቸው። ይህም በፖለቲካ ውስጥ ሴቶች ጥሩ በሚንቀሳቀሱባቸው ሃገራት ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ውጤታማነታቸው ከፍ ያለ መሆኑን ያሳያል።

ሆኖም በሴት መሪዎች እና የተሻለ ህይወት አኗኗርን ለሌሎች ሴቶች በመፍጠር በኩል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ማወቅ ከባድ ነው። ሴት መሪዎች ኖሩም አልኖሩም ባለፉት አስር ዓመታት በብዙ ሃገራት የጾታ እኩልነት በመሻሻል ላይ መገኘቱ አንድ ምክንያት ነው።

በተጨማሪም በቅርቡ ወደ ስልጣን የመጡም ሆኑ ስልጣን ከያዙ ጥቂት ጊዜያትን ያስቆጠሩ ሴት መሪዎች ፖሊሲዎቻቸው ያለውን ተጽእኖ ለመለካት ከባድ ነው።

ሆኖም ሴት መሪዎች በአካባቢያቸው የሚኖሩ ሴቶችን ተስፋ የሚያሳድጉ ከመሆኑም በላይ ሃገሮቻቸውም ለሴት ዜጎቻቸው የተሻለ ህይወት ያቀርባሉ።

ተያያዥ ርዕሶች