ከአጥፍቶ ጠፊ ጋር ተባብራለች የተባለችው ኢትዮጵያዊት ከስራዋ ተባረረች

ሙሉ እመቤት Image copyright Met Police

በእንግሊዝ ሳውዝ ዋርክ አስተዳደር ከ2013 ጀምሮ ተቀጥራ ስትሰራ የነበረቸው ሙሉእመቤት ግርማ የቦምብ ጥቃት ሊፈጽም የነበረ ወንጀለኛ እንዲያመልጥ በመርዳት ወንጀል ጥፋተኛ መባሏ ከታወቀ በኋላ ከስራዋ ተባራለች።

ሙሉእመቤት በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2005 የምድር ውስጥ ባቡር መንገዶኞች ላይ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ሊፈጽም አቅዶ የከሸፈበት ሁሴን ኦስማን እንዲጠፋ ረድታዋለች በሚል ተከሳ ነበር።

በ 2008 ደግሞ ፍርድ ቤቱ ከጥቃት ፈጻሚው ጋር በመተባበርና በአጥፍቶ መጥፋት ሙከራው የነበረውን ሚና በተለመከተ መረጃ ባለማቅረቧ ጥፋተኛ ሆና አግኝቷቷል።

ለጥፋቷም የ10 ዓመታት እስር ሲበየንባት የ24 ዓመት ወጣት ነበረች፤ ከይግባኝ በኋላ ግን እስሩ ወደ 5 ዓመት ተቀንሶላት ነበር።

ፍርድ ቤቱ ግለሰቡ ወደተያዘባት ሮም ከመግባቱ በፊት ወደብራይተን እንዲያመልጥ አግዛዋለች ብሏል።

የታሰረችውም የኦስማን ባለቤት ከሆነችው ከእህቷ የሺ ግርማ ጋር ነበር።

Image copyright Met Police
አጭር የምስል መግለጫ ሁሴን ኦስማን

ሙሉ አመቤትም ይህንን የእስር ጊዜዋን አጠናቃ በ2013 በሳውዝ ዋርክ ምክርቤት የሰልጣኞች ረዳት ሆና ተቀጠረች።

ዘ ሰን እንደሚለው የ33 ዓመቷ ሙሉ እመቤት የምክር ቤቱ የተግባር ልምምድ መርሃግብር በስኬት መጠናቀቁን በሚያበስረው የመጽሄቱ የፊት ገጽ ላይም ወጥታ ነበር።

ሆኖም ለቀጣሪዎቿ ያለባትን የወንጀል ሪከርድ ሳትነግር ብትቆይም እነርሱ ግን ባወቁበት ቅጽበት ከስራዋ አባረዋታል።

'የቆይታዋ ግምገማ'

የምክር ቤቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤሌኖር ኬሊ '' ልክ የኋላ ታሪኳን እንዳወቅን ቅጥሯን ሰርዘነዋል '' ብለዋል።

''እርሷ ግን ለምክርቤቱ ስለፈጸመችው ወንጀል አልተናገረችም''

በተቀጠረችበት ጊዜም የፖሊስ ክትትል የሚደረግባቸው ሰዎችን ዝርዝር መረጃ የማየት እድሉ አልነበራትም።

ምክር ቤቱ ተቀጣሪ እያለች የኮምፒዩተር አጠቃቀሟን ጨምሮ የነበራትን እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በጥልቀት ቢመረምርም ምንም አይነት ትክክል ያለሆነ ነገር አልፈጸመችም።

Image copyright Met Police
አጭር የምስል መግለጫ ኦስማን እ.አ.አ ሐምሌ 2007 በግድያ ሴራ የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖበታል

ኦስማን ከሙክታር ሰኢድ ኢብራሂም፣ ኬኣሲን ኦማር እና ራምዚ ሞሃመድ በተለያዩ የመሬት ውስጥ የባቡር ጣቢያዎችና በአውቶቡስ ላይ ጥቃት ለመፈፀም በፈንጂ የተሞሉና በጀርባ የሚታዘሉ ቦርሳዎችን ለመስጠት ሞክሯል። ነገር ግን ቦምቦቹ ሳይፈነዱ ቀሩ።

ከጥቃቱ ሙከራ በኋላ ሰዎችን ለመግደል በማሴር ወንጀል ተከሰው እአአ በ2007 የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

የጥቃቱ ሙከራ የተደረገው አራት አጥፍቶ ጠፊዎች በማዕከላዊ ለንደን በፈፀሙት ጥቃት 52 ሰዎች የሞቱበትና ከ770 በላይ ሰዎች ከቆሰሉ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነበር።