ራይላ ኦዲንጋ ከኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እራሳቸውን አገለሉ

ራይላ ኦዲንጋ Image copyright SIMON MAINA

የኬንያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሊካሄድ ታቅዶ ከነበረው ምርጫ እራሳቸውን አግልለዋል።

ራይላ ኦዲንጋ ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋል በማለት ነው ከምርጫው የወጡት።

ባለፈው ነሐሴ ተካሂዶ በነበረው ምርጫ የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን፤ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምርጫውን እንዳሸነፉ ቢያውጅም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ግን ውጤቱን መሰረዙ ይታወሳል።

ኬንያ ድጋሚ ምርጫ እንድታካሂድ ፍርድ ቤት ወሰነ።

ራይላ በንግግራቸው ''የኬንያ ህዝብ፣ የአካባቢውን እና የዓለም ፍላጎትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከምርጫው እራሴን ማግለሌ ትክክል ነው'' ብለዋል።

ራይላ ኦዲንጋ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ጥሪ ''የምርጫ ማሻሻያ ከሌለ ምርጫ የለም'' የሚል መፈክር ይዘው ነገ ረቡዕ ወደ አደባባይ እንዲወጡ ቀስቅሰዋል።

በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ቮኢ በምትባል ከተማ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ''ወደ ምርጫ ለመመለስ ምንም ችግር የለብንም። ከባለፈው ምርጫ የበለጠ ብዙ ድምፅ እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን'' ብለዋል።

የድጋሚ ምርጫው ጥቅምት 16 እንዲካሄድ ቀጠሮ ተይዞ ነበር።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ