ቀጣዩ የኬንያ የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?

ኡሁሩ ኬንያታ እና ራይላ ኦዲንጋ

የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነሐሴ 2 ተካሂዶ በነበረው ምርጫ ተሳትፈው የነበሩ ዕጩዎች ዳግም በሚደረገው ምርጫ ላይ መሳተፈ ይችላሉ ሲል ውሳኔ አስተላለፈ።

ይህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የመጣው ከአንድ ቀን በፊት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ ከምርጫው ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ ነው።

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ያሸነፉበት የምርጫ ውጤት ተሰርዞ ዳግም ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ ያስተላለፈው የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነበር።

ይሁን እንጂ ራይላ ኦዲንጋ ''ምንም የተቀየረ ነገር የለም ስለዚህ ተመሳሳይ ስህተት ሊፈፀም ይችላል በማለት'' እራሳቸውን ከምርጫው አግልለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢቃወሙትም የኬንያ ፓርላማ በምርጫ ህጉ ላይ በርካታ ማሻሻያዎችን አድርጓል።

ዳግመኛ ምርጫው ይካሄዳል?

አዎን ይካሄዳል።

በህገ-መንግሥቱ መሰረት ቀጣዩ ምርጫ ጥቅምት 22 ይካሄዳል።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንደሚያሳየው ምንም እንኳ ራይላ ኦዲንጋ እራሳቸውን ከምርጫው ቢያገሉም ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ሁሉም ተፎካካሪዎች እራሳቸውን እስካላገለሉ ድረስ መወዳደር ይኖርባቸዋል። ይህ ማለት ደግሞ ከራይላ ኦዲንጋ ውጪ የነበሩት ሌሎች ተፎካካሪዎች በባለፈው ምርጫ አግኝተው የነበረው ድምፅ ከ1% በታች ስለነበር የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ዳግመኛ መመረጥ እድል ከፍተኛ ነው።

በመጀመሪያ ታቅዶ የነበረው ዳግመኛ ምርጫ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ እና ራይላ ኦዲንጋን ብቻ የሚያሳትፍ ነበር።

ራይላ ኦዲንጋ ከምርጫው እራሳቸውን ለምን አገለሉ?

የተለያዩ ፓርቲዎች ስብስብ መሪ የሆኑት ኦዲንጋ ምክንያታቸውን ሲያስረዱ ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ያስቀመጥናቸው መስፈርቶች አልተሟሉም። የምርጫ ኮሚሽኑም አስፈላጊውን ማሻሻያ እንዲያደርግ በቂ ጊዜ ያስፈልገዋል ይላሉ።

ራይላ ኦዲንጋ የሚመሩት ጥምር ፓርቲ ጥያቄዎች፤

•ነሐሴ 2 ተካሂዶ የነበረውን ምርጫ እንዲዛባ አድርገዋል ያሏቸውን የምርጫ ሃላፊዎች ይባረሩ።

•በባለፈው ምርጫ የድምፅ መስጫ ካርዶችን እና የድምፅ ሰጪዎችን ሲያጣሩ የነበሩ ድርጅቶች ይቀየሩ።

•ዓለም አቀፍ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ከምርጫ ኮሚሹኑ ጋር በጋራ ሆነው ውጤቱ እንደይጭበረበር እንዲሰሩ።

የምርጫ ኮሚሽኑ የቀየረው ነገር አለን?

ፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ውድቅ ከተደረገ በኋላ የምርጫ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ዋፉላ ቼቡካቲ ቡድናቸው ላይ ለውጥ እንደሚያደርጉ ቃል ቢገቡም ከሌሎች ኮሚሽነሮች እንቅፋት ገጥሟቸዋል።

ቼቡካቲ የዳግም ምርጫውን የሚከታተል አዲስ ቡድን ቢያቋቁሙም ከሌሎች ኮሚሽነሮች ጋር እንዴት እንደሚሰራ እና ያለው ስልጣን አልታወቀም።

የምርጫ ኮሚሽኑ በቀዳሚው ምርጫ የሚረዱትን ግብዓቶች ካቀረበለት ድርጅት ጋር ውል ያለው በመሆኑ ሌላ ድርጅት ስራውን እንዲያከናውን ለማድረግ እንደማይችል ይፋ አድርጓል።

ኦዲንጋ በምርጫው እንደማይሳተፉ ካሳወቁ በኋላ ኮሚሽኑ ወደፊት አቅጣጫውን በተመለከተ ከህግ ባለሙያዎች ጋር እንደሚመካከር አስታውቋል።

የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ፓርቲ ምን ይላል?

ገዢው ጁቢሊ ፓርቲ በምርጫው ያለው ተሳትፎ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በፓርላማው ያለውን የበላይነት ተጠቅሞም አወዛጋቢውን የምርጫ ህግ ለማሻሻያ ከጫፍ ደርሷል። ማሻሻያው የምርጨ ማጭበርበርን ለመከላከል የተቀመጡ አሰራሮችን ይቀይራል የሚል ፍራቻ አለ።

ማሻሻያው ካካተታቸው ጉዳዮች መካከል፡

•በቀጣይ የምርጫ ውጤቶች የማይቀበል ችግር መፈጠሩን ማሳመን ይጠበቅበታል

•የምርጫ ኮሚሽን ሊቀመንበር ለመሆን ቢያንስ ለ15 ዓመታት አንጋፋ ዳኛ ወይም ጠበቃ ሆነው ያገለገሉ መሆን ይኖርባቸዋል የሚለውን ማስቀረት። ይህ ደግሞ የአሁኑን ሊቀመንበር በማንሳት ለገዢው ፓርቲ ቅርብ የሆነ ሰው ለመሾመ የተደረገ ነው በሚል ትችት ቀርቦበታል።

•የምርጫ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሉ ለሙሉ ድምጽ ተቆጥሮ ባያልቅም የቀረው ድምጽ ውጤቱ ላይ ምንም አይነት ለውጥ የማያመጣ ከሆነ አሸናፊውን ማብሰር ይችላል የሚሉት ይገኙበታል።

አወዛጋቢው የምርጫ ህግ ማሻሻያ ከተቃዋሚ ፓርቲው በተጨማሪ በሃይማኖት መሪዎች፣ የሠብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ አሜሪካ እና እንግሊዝን ጨምሮ በሌሎች ምዕራባዊያን ዲፕሎማቶች እና የምርጫ ኮሚሽኑ ጭምር ትችት ቀርቦበታል።

ማሻሻያው የተደረገበት ጊዜ ለድጋሚው ምርጫ ከመቅረቡም በላይ እየተደረገ ካለው ዝግጅት ጋር አብሮ አይሄድም የሚል ትችትም ቀርቦበታል።

ማሻሻያው እስካሁን ተግባራዊ መሆን ባይጀምርም ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በፊርማቸው እንደሚያጸድቁት አስታውቀዋል።

ገዢው ጁቢሊ ፓርቲ ማሻሻያው ያስፈለገው ባለፈው ነሐሴ ተደርጎ ውድቅ የተደረገው አይነት የምርጫ ክፍተት እንዳይደገም ያደርጋል በሚል ትችቱን እየተከላከለ ይገኛል።

በቀጣይ ምን ይፈጠራል?

የተቃዋሚ ጥምር ፓርቲ የሆነው ናሳ "ለውጥ ከሌለ ምርጫ የለም" በሚል መፈክር አዲስ ተቃውሞ ደጋፊዎቹን ወደ አደባባይ እየጠራ ሲሆን ገዢው ጁቢሊ ፓርቲ በበኩሉ ምርጫ ቅስቀሳው መግፋቱን ተከትሎ፤ በድጋሚ አመጽ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ