የህንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያለ ዕድሜ ጋብቻን መደፈር ነው ብሎ ደነገገ

በህንድ ውስጥ ህፃናትን መዳር የተለመደ ነው Image copyright Getty Images

የህንድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንዶች በዕድሜ ካልደረሱ ሚስቶቻቸው ጋር ግንኙነት መፈፀምን ይፈቅድ የነበረውን አንቀፅ ውድቅ አድርጓል።

ይህ አከራካሪ የተባለው አንቀፅ የመደፈር ህግ አካል ሲሆን በጋብቻ ውስጥ አንድ ወንድ 15 ዓመት ዕድሜ ካላት ሴት ጋር ግንኙነት ማድረግን ይፈቅዳል።

ምንም እንኳን በህንድ ህግ የጋብቻ እድሜ 18 ዓመት ቢሆንም በጋብቻ ውስጥ መደፈር እንደ ወንጀል (ጥፋት) አይታይም።

ይህ ውሳኔ የተለያዩ የሴት መብት ተሟጋቾችን ያስደሰተ ቢሆንም፤ አንዳንድ ታዛቢዎች ትዕዛዙን ለማስፈፀም አስቸጋሪ እንደሆነ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ውሳኔውም እንደሚያትተው ከ18 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ሴቶች ባሎቻቸውን በመድፈር ለመክሰስ የሚያስችላቸው ሲሆን፤ በአንድ ዓመት ውስጥም ተገደው ግንኙነትን እየፈፀሙ መሆናቸውን ማሳወቅ አለባቸው።

"ይህ ምሳሌያዊ ውሳኔ ለዓመታት በሴት ልጆች ላይ ተጭኖ የነበረውን ታሪካዊ ኢ-ፍትሀዊነትን የቀየረ ነው። እንዴት ጋብቻ እንደ መስፈርት ሆኖ ሴት ልጆች ላይ አድልዎ መፈፀሚያ መሳርያ ይሆናል?" በማለት ለቢቢሲ የተናገሩት ቪክራም ሲርቫስታቫ አንቀፁን ለማስቀየር ፊርማ ሲያሰባስቡ ከነበሩት አንደኛው ናቸው።

ነገር ግን በደልሂ የቢቢሲ ዘጋቢ እንዳለቸው፤ በርካቶች ዜናውን በደስታ ቢቀበሉትም የህፃናት ጋብቻ በአገሪቷ በተስፋፋበት ሁኔታ ህጉን ማስፈፀም አስቸጋሪ ነው በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች።

"ፍርድ ቤትም ሆነ ፖሊስ በእያንዳንዱ ግለሰብ መኝታ ክፍል እየገቡ ሊቆጣጠሩ ይችሉም። እንዲሁም በቤተሰቦቿ ፈቃድ የተዳረች ሴት ልጅ ፖሊስ ወይም ፍርድ ቤት ሄዶ ባሏን ለመክሰስ ድፍረቱ አይኖራትም" በማለት የቢቢሲ ዘጋቢ ትናገራለች።

የህንድ መንግስት በበኩሉ የህፃናት ጋብቻ ለልማት፤ ረሃብና ድህነትን በማጥፋት፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን በማሳደግ፣ የፆታዎች እኩልነትን በማስፈን፣ የህፃናትን ደህንነት መጠበቅ እንዲሁም የሴቶችን ጤና በማሻሻል በኩል መሰናክሎችን እየፈጠረ ነው በማለት ይናገራሉ።