በአምስት ሰንጠረዦች የቻይናን ዜጎችን ይበልጥ ይረዱ

Title graphic

ባለፉት 5 ዓመታት ፕሬዝዳንት ዢ ሺንፒንግ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የቻይን የሃብት መጠን እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ጨምሯል። ይህ የሃገሪቷ እድገት እና ሃብት መጨመር በተራው የቻይና ቤተሰብ ህይወት ላይ ምን አይነት ለውጥ ያመጣል?

የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት የቻይና ቀጣይ 5 ዓመታት ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ሲሰበሰቡ፤ የቻይናውያን ህይወት እንዴት እየተቀየር እንደሆነ ከአምስት ነጥቦች አንፃር እንመልከት።


የቻይናን ህዝብ ቁጥር ለመመጠን ተግባራዊ ተደርጎ የነበረው ቻይናውያን አንድ ልጅ ብቻ እንዲወልዱ የሚያሰገድደው ፖሊሲ የፆታ ልዩነትን ከፈጠረ በኋላ እአአ በ2015 እንዲቀር ተደርጎ ነበር። በአሁኑ ወቅት በቻይና ቤተሰብ መስርቶ ከአንድ በላይ ልጆችን መውለድ ቢቻልም፤ የሚፈፀሙ ጋብቻዎች ቁጥሩ ግን ከሌሎች ካደጉት ሃገራት ጋር ተመሳሳይ ነው። ትዳር የሚመሰርቱ ሰዎች ቁጥር ሲቀንስ የሚፋቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ጨምሯል።

ይህ እንዳለ ሆኖ ዛሬም ቢሆን ቻይና ከአሜሪካ እና ከምዕራብ አውሮፓ ሃገራት ያነሰ የፍቺ ቁጥር ነው ያላት።


ከቁጥር አንፃር በፆታዎች መካከል ሰፊ ልዩነትን አስከትሎ እንዲቀር የተደረገው 'የአንድ ልጅ ፖሊሲ' በወደፊቷ ቻይና ላይ ችግር ማስከተሉ አይቀሬ ነው የሚል ስጋት አለ።

በቻይና እድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ ሆኖ ያላገቡ በርካታ ዜጎች አሉ። እንደዚህ አይነት ወንዶች መጠሪያ ስምም አላቸው፣ 'ሼግናን' ይባላሉ የተረፉ ወንዶች እንደማለት ነው።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት ሉዊስ ኩይጅስ፤ በሃሪቷ ተተግብሮ የነበረው 'የአንድ ልጅ ፖሊሲ' የቻይናን ከፍተኛ የወሊድ እና የሞት መጠንን ወደ ዝቅተኛ የወሊድ እና ሞት መጠን አሸጋግሮታል ሲሉ ያስረዳሉ።

የወሊድ መጠን መቀነሱ እና በእድሜ የገፉ ዜጎች መብዛታቸው በቻይና የሰው ኃይል ላይ እና ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ሲሉ ባለሙያው ያብራራሉ።

'የአንድ ልጅ ፖሊሲ' እንዲቀር ቢደረግም የወሊድ መጠን ሊያንስራራ የሚችለው ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ነው ሲሉ ሉዊስ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።


እአአ በ2000 ገደማ የተወለዱ ቻይናውያን ከአሜሪካ እና አውሮፓውያን ወጣቶች በላይ የቤት ባለቤት ናቸው። ንፅፅሩን ቀጥሎ ካለው ሰንጠረዡ ይመልከቱ።

ቻይናውያን በእድሜ ተቀራራቢ ከሆኑ ከሌሎች ሃገራት በተለየ የቤት ባለቤት ከሆኑባቸው ምክንያቶች መካከል ዶ/ር ጄዩ ሊዩ ለቢቢሲ ሲያስረዱ ''ቻይናውያን ወላጆች በተቻላቸው አቅም ወንድ ልጆቻቸውን የቤት ባለቤት የማድረግ ልማድ አላቸው። ይህም ወንዱ ልጅ ትዳር እንዲመሰርት ያግዛዋል። ብዙ የፍቅር ታሪኮች መጨረሻቸው የማያምረው ወንዱ የመኖሪያ ቤት ማቅረብ ካልቻለ ነው'' ይላሉ።


አማካይ የቻይናውያን ገቢ በፍጥነት መጨመሩ እንደቀጠለ ነው።

ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ቻይናውያን ለምግብ የሚያወጡት ወጪ ሲቀንስ፤ ለጤና፣ ለአልባሳት፣ ለመጓጓዣ እና ለመገናኛ ዘዴዎች በተለይ ለተንቀሳቃሽ ስልክ የሚያወጡት ገንዘብ ጨምሯል።

ቻይናውያን የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለመገናኛ ዘዴነት ይጠቀማሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመፈፅም ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን ይጠቀማሉ።

'ዊቻት' የሚባለው መተግበሪያ በቻይና የተጠቃሚዎቹ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በሃገሪቱ ህይወት ያለ ተንቀሳቃሸ ስልክ የማይታሰብ የስመስሎታል ይላሉ የቴክኖሎጂ ተንታኙ ዱካን ክላርክ።


በቻይና አማካይ የገቢ መጠን መጨመር ለትምህርት ከሚወጣው ወጪ ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ አለው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ልጆቻቸውን ወደ ውጪ ሃገራት ልከው የሚያስተምሩ ቤተሰቦች ቁጥር ጨምሯል።

ከሌሎች ሃገራት ተማሪዎች በተለየ መልኩም ቻይናውያን ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ሃገራቸው ይመለሳሉ።

ዓለም አቀፍ ድግሪ ያላቸው እና በሌሎች ሃገራት የኖሩ ቻይናውያን ብዛት በጨመረ ቁጥር ቀጣዩ የቻይና ሥርዓት 'በዓለም አቀፋዊ አስተሳስብ' የተቃኘ እንዲሆን ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ በቀጣይ አስር ዓመታት ውስጥ በምጥኔ ሃብታዊ አቅሟ ቁጥር አንድ የምትሆነውን ቻይና ይተሻለ ቦታ ላይ አንድትቀመጥ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።