የተቃውሞ ሰልፎች እንዳይካሄዱ የኬንያ መንግሥት ከለከለ

ተቀዋሚ ሰልፈኞች
አጭር የምስል መግለጫ የተቃውሞ ሰልፎች በዋና ዋና ከተሞች ውስጥ በሚገኙ የንግድ አካባቢዎች አቅራቢያ ማድረግ አይቻልም ተብሏል

ተጠባባቂ የሃገር ውስጥ ደህንነት ሚንስትር የሆኑት ፍሬድ ማቲያንጊ ''ሰልፎቹን ማስቆም ያስፈለገው በንብረት እና በንግድ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት ለማስቆም ነው'' ብለዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምር የሆነው ናሳ በምርጫ ኮሚሸኑ ውስጥ ማሻሻያዎች እንዲካሄዱ ጫና ለማሳደር በተለያዩ የሃገሪቷ ክፍሎች ውስጥ የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያካሂድ ቆይቷል።

የደህንነት ሚንስትሩ እንዳሉት፤ ካሁን በኋላ በተቃውሞ ሰልፎች ወቅት ለሚከሰት ማንኛው አይነት ጥፋት የሰልፎቹ አዘጋጆች ተጠያቂ ይሆናሉ።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ከዚህ በፊት በጠሩት ስልፍ ምክንያት የቀረበባቸውን ክስ ፍርድ ቤት ቀርበው ይከላከላሉ ብለዋል።

''ካሁን በኋላ በናይሮቢ፣ ሞምባሳ እና ኪሱሙ ንግድ ቀጠናዎች የተቃውሞ ሰልፎችን ማድረግ አይቻልም። መንግሥት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን እየተጋፋ አይደለም። ይሁን እንጂ ሰልፈኞቹ የሌሎች ኬንያውያንን መብት መጋፋት አይችሉም'' ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሚንስትሩ በተቃውሞ ሰልፎቹ ወቅት ንብረታቸው የወደመባቸው ወይም የተዘረፉ ዜጎች የጠፋባቸውን ንብረት ፖሊስ ዘንድ ቀርበው እንዲያስመዘግቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ መንግሥትም የደረሰውን የጉዳት መጠን በማወቅ ጥፋተኞቹን ለህግ ያቀርባል ብለዋል።

ፕሬዝዳንታዊው ምርጫ በድጋሚ እንዲካሄድ ከተወሰነ በኋላ ተቃዋሚው ፓርቲ ናሳ የምርጫ ኮሚሽን ባለሥልጣናት ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ በመጠየቅ በተለያዩ ቀናት ተቃውሞ ሰልፎች እንዲካሄዱ ሲያበረታታ ነበር።

ራይላ ኦዲንጋ ጥያቄያቸው ተግባራዊ ባለመሆኑ በድጋሚ ምርጫው እንደማይሳተፉ ካሳወቁ በኋላ ተቃውሞው ተባብሶ ነበር።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ