''አባቴ በመንገድ ላይ እየተጓዘ ነበር በጥይት ተመትቶ ህይወቱ ያለፈው''

ኢትዮጵያ Image copyright Google

የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ትላንት በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ማን እንደጠራቸው ባለታወቁ ሰልፎች ላይ የስድስት ሰዎች ህይወት አልፏል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት እንዳረጋገጠው በትላንትናው ዕለት በተለያዩ የክልሉ ከተሞች በነበሩ ሰልፎች የስድስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ33 በላይ በሚሆኑት ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሷል።

ከሟቾቹ መካከል ሶስቱ በሻሸመኔ ከተማ ነው ህይወታቸው ያለፈው።

በዚሁ ከተማ ከተገደሉት መካከል የ67 ዓመት አዛውንት የሆኑት አቶ ገለቶ ገነሞ ይገኙበታል። አቶ ገለቶ በሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ የሆነውን ልጃቸውን ሃምዳ ገለቶን ለመጠየቅ ከገጠር መጥተው ነበር በትላንትናው ዕለት በጥይት ተመተው ህይወታቸው ያለፈው። ሃምዳ ለቢቢሲ እንደተናገረው ''አባቴ መንገድ ላይ በነበረበት ጊዜ ምንም ዓይነት ተቃውሞ አልነበረም። መንገድ ላይ እየተጓዘ ነበር ከመኪና ላይ በተተኮሰበት ጥይት ተመትቶ ህይወቱ ያለፈው'' ብሏል።

ለደህንነቱ ሲባል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ሌላ ተጎጂ እጁ ላይ በጥይት ተመቶ ጉዳት እንደረሰበት ለቢቢሲ ተናግሯል። ''በመጀመሪያ በድንጋይ የተመታሁ ነበር የመሰለኝ አትኩሬ ስመለከት ነው በጥይት እንደተመታሁ የተረዳሁት። በድንጋጤ ስሜት ውስጥ ሆኜ ወደኋላ ዞሬ ሳይ አንድ የመከላከያ ሠራዊት አባል የጫነ ፓትሮል መኪና ተመለከትኩ። በገቢና ውስጥ ሌሎች ሊኖሩ ይችላሉ እኔ ግን አላየሁ'' ብሏል።

በሰልፉ ላይ ተሳታፊ የነበረው ይህ ወጣት ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሃዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል እንደተላከ ነግሮናል።

የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ ጠይባ ሃሰን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ትላንት በነበረው ሰልፍ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠዋል። ወ/ሮ ጠይባ ለሁለት ወጣቶች እና ለአንድ አዛውንት መሞት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት እና አንድ የሃገር መከላከያ ሠራዊት አባል በሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ቁጥጥር ስር ይገኛሉ ብለዋል።

Image copyright Addisu Arega

'ማን እንደጠራው ያልታወቀው ሰልፍ'

በትላንትናው ዕለት በሻሸመኔ፣ በምዕራብ ሃረርጌ በቦኬ ወረዳ፣ በአምቦ እና በሌሎች በርካታ ቦታዎች ላይ ሰልፎች ተካሂደው እንደነበር የክልሉ ኮሚኒኬሸን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በሻሸመኔ እና በቦኬ ወረዳ ካጋጠሙ ችግሮች ውጪ በሌሎች ቦታዎች የተካሄዱት ሰልፎች በሰላም ተጠናቀዋል ብለዋል። አቶ አዲሱ እንዳሉት ማን እንደጠራቸው ባለታወቁት ሰልፎች ላይ የስድስት ሰዎች ህይወት አልፏል፤ ከ 30 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ተጎድተዋል።

እንደ አቶ አዲሱ ከሆነ አሁን እየተለመዱ የመጡት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትን እንደግፋለን በማለት የሚጠሩ ሰልፎች ናቸው። ''አሁን እየተጠሩ ያሉት ሰልፎች ሰላማዊ ሰልፎች አይደሉም። ሌላ ተልዕኮ ያላቸው ሰልፎች ናቸው'' ብለዋል ኃላፊው።

"የተካሄዱት ሰልፎች ህጋዊም ይሁኑ ህገ-ወጥ ባዶ እጅ በወጡ ዜጎች ላይ ተኩስ ከፍተው ህይወት ያጠፉና አካል ያጎደሉ በሃገሪቷ ህግ ይጠይቃሉ" ብለዋል።

ዛሬም በጉደር እና ወሊሶ ከተሞች ሰልፎች ተካሂደዋል።