ፍልስጤማውያኑ ሃማስና ፋታህ ስምምነት ላይ ደረሱ

Hamas runs Gaza and Fatah controls the West Bank Image copyright AFP

የፍልስጤሙ ቡድን ሃማስ ከፋታህ ጋር ለአስር ዓመታት የዘለቀውን አለመግባባት ለማብቃት ከስምምነት ላይ መድረሱን አሳወቀ።

የጋዛ ሰርጥን የሚቆጣጠረው ሃማስ የስምምነቱን ዝርዝር ይፋ እነደሚያደርግ አስታውቋል። ነገር ግን ፋታህ ስለስምምቱ ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተካሄደውን የእርቅ ውይይት ግብፅ ስታደራድር ቆይታለች።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል በ2007 (እአአ) የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ግጭት ተከትሎ በጋዛ እና በምዕራብ ዳርቻ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን በቡድኖቹ በተናጠል እየተዳደሩ ይገኛሉ።

ለሃማስ ቅርብ መሆኑ የሚነገርለት የፍልስጤማውያን የመረጃ ማዕከል ስለስምምነቱ ዝርዝር ዛሬ ካይሮ ላይ መግለጫ እንደሚሰጥ አሳውቋል።

የሃማስ ቃል አቀባይ ሳሚ ኣቡ ዙህሪ እንደተናገሩት ካይሮ ውስጥ የተካሄዱት የሁለቱ ቡድኖች ውይይት ''ጥልቅና ጠንካራ'' ነበር ብለዋል።

''ውይይቶቹ አውንታዊ የነበሩ ሲሆን፤ ግብፃውያኑም ገለልተኛ ነበሩ'' ሲሉ ለፍልስጤማውያን የመረጃ ማዕከል ተናግረዋል።

ባለፈው ወር ሃማስ ጋዛን የሚያስተዳድረው ኮሚቴ ሥራውን እንዲያቆም ማድረጉ ይታወሳል።

ይህ እርምጃም የምዕራብ ዳርቻ አካባቢዎችን የሚያስተዳድረውና በፋታህ የሚመራው የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ያቀረቡት ቁልፍ ቅድመ ሁኔታ ነበር።

የፍልስጤም አስተዳደር ጠቅላይ ሚኒስትር ራሚ ሃምዳላህ ባልተለመደ ሁኔታ ባጋዛ ሰርጥ ጉብኝት አድርገዋል።

እንዳሉትም የፍልስጤም አስተዳደር ባለሥልጣን የጋዛን አስተዳደራዊ ጉዳዮችና የድህንነት ሃላፊነቶችን ይሰወዳል ብለዋል።

እስራኤል፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ዩናይትድ ኪንግደምና ሌሎች ሃገራት መላው ሃማስን አንዳንድ ጊዜም ወታደራዊ ክንፉን ሽብርተኛ ቡድን ብለው ሰይመውታል።