ትራምፕ፡ የኢራን የኑክሊዬር ስምምነትን አቋርጣለሁ

አሜሪካ የኑክሊዬር ስምምነቱን እንድታከብር ተቃዋሚዎች ገለፁ Image copyright Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የነበረውን የኑክሊዬር ስምምነት በማቋረጥ ፊት ለፊት መጋፈጥ የሚያስችል ዕቅድ እንደሚነድፉ ይጠበቃል።

አሜሪካ ስምምነቱን ከመሰረዟ በፊት ለኮንግረሱ 60 ቀናትን በመስጠት እንደገና ማዕቀብ ይጣል አይጣል የሚለውን የሚወስኑበት ይሆናል።

በዚህም ጉዳይ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን ከአውሮፓና ከቻይና አቻዎቻቸው ጋር እየመከሩ እንደሆነ ባለልስልጣናት ይናገራሉ።

የኑክሊዬር ስምምነቱ እንዳይሻር በአሜሪካ ውስጥና በውጭ አገራትም ትራምፕ ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ እየተሞከረ ነው።

ከሁለት ዓመታት በፊት በነበረው ስምምነት መሰረት ኢራን የኑክሊዬር ፕሮግራሟን ለማቆምና በተወሰነ መንገድ የተጣለባት ማዕቀብ የሚነሳበት ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር የሚታወስ ነው።

ትራምፕ በተደጋጋሚ ስምምነቱ ላይ ከፍተኛ ትችት ከማቅረብ በተጨማሪ በምርጫ ዘመቻቸውም ወቅት ይህንን ስምምነት እንደሚያስወግዱትም ቃል ገብተው ነበር።

ኮንግረሱ በየሦስት ወራት ኢራን የስምምነት ቃሏን መጠበቋን የሚያረጋግጥ ሲሆን ትራምፕም ሁለት ጊዜ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ትራምፕ ስምምነቱን ላይከተሉ ይችላሉ የሚሉት ጥርጣሬዎች በአሜሪካ ደጋፊ አገራትና በአንዳንድ አስተዳደሩ አባላት መደናገጥን ፈጥሯል።

መከላከያ ሚኒስትሩ ጀምስ ማቲስ በዚህ ወር መጀመሪያ ለሴኔቱ ስምምነቱን ወደጎን መተው ከአገራዊ ፍላጎት ጋር አይጣጣምም ብለዋል።

ትራምፕ የኢራንን የኑክሊዬር ስምምነትን "መጥፎ ስምምነት" በማለት ለመሰረዝ ዝተዋል።

በአሜሪካ ህግ መሰረት ይሄንን ስምምነት ለማስተካከል ኢራን የተወሰነውን የስምምነቱን አካል እንዳላከበረችና የነበረው ማዕቀብም እንዲቀጥል መረጃ መቅረብ ይኖርበታል።

እንደገና ማዕቀብ የመጣሉን ሁኔታ በህግ አውጭዎቹም የሚወሰን ይሆናል።

የስምምነቱ ተችዎችም ቢሆኑ ኢራን ስምምነቱን ባላፈረሰችበት ሁኔታ አሜሪካ ስምምነቱን ብትጥስ ተአማኒነቷን ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተው የይናገራሉ።

የሪፐብሊካን ፓርቲ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀ መንበር ኤድ ሮይስ ስምምነቱ ችግር ያለበት ቢሆንም ልንተገብረው ይገባል ብለዋል።

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይና የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም ትራምፕ በስምምነቱ እንዲቀጥሉም መክረዋል።

ትራምፕ በተደጋጋሚ ኢራን የስምምነቱን "መንፈስ" ሰብራዋለች ቢሉም፤ የዓለም አቀፍ አውቶሚክ ኤጀንሲ በዚህ አይስማማም በተቃራኒው ኢራን ስምምነቷን እንዳከበረች እያለ ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት የተደረገው ስምምነት ኢራን የኑክሊዬር መሳሪያዎችን ምርት እንድታቆም የሚል ሲሆን፤ በምላሹም ዓለም አቀፍ የዘይት ሽያጭ እንዳታደርግ ይከለክላት የነበረው ማዕቀብ ተነስቶላታል።

ሙሉ በሙሉ የማዕቀቡ መነሳት በኢራን ላይ የሚወሰን ሲሆን፤ የዩራንየም ክምችቷን መቀነስ እንዲሁም መርማሪዎች አገሪቷ ውስጥ እንዲገቡ መተባበርን ይመለከታል።