ካለሁበት 5፡ 'ኑሮዬን ቶሮንቶ ያደረግኩት በአጋጣሚ ነበር'

Image copyright Rebecca Teshome
አጭር የምስል መግለጫ ርብቃ፣ በበዓል ቀን ከቤተሰብ ጋር በተሰባሰቡበት ዕለት

እኔ ርብቃ ተሾመ ነኝ የምኖረውም በካናዳ ቶሮንቶ ነው። ኑሮዬን ቶሮንቶ ላደርግ የቻልኩት በአጋጣሚ ነበር። አብሮኝ ይሠራ የነበረ ሰው ከሕንድ ወደ ካናዳ ነዋሪነቱን ሲቀይር እኔም ወደ ካናዳ እንድሄድ በጣም ገፋፋኝ ።ለመሥራት ያለኝን አቅምና ችሎታዬን ማሳደግ የምችልበት አገር እንደሆነም በተደጋጋሚ ይነግረኝ ነበር። በየጊዜው ይወተውተኝ ስለነበረ እንዲተወኝ ብቻ ወረቀቱን ሞልቼ የመኖሪያ ፈቃድ ሲደርሰኝ ነው ወደ ካናዳ ያቀናሁት።

ጊዜው እ.አ.አ 1990 ነበር፣ ያኔ ደግሞ ወደ ካናዳ ለመግባት ናይሮቢ ወደሚገኘው የካናዳ ኤምባሲ ደብዳቤ መጻፍ ብቻ ነበር የሚጠበቀው። ደብዳቤውንም ከተጻጻፍኩ በኃላ፣ የመኖሪያ ፈቃድ እንደተሰጠኝ ጊዜው የሚያበቃበትን ቀን አረጋግጬ ከመቃጠሉ ከአሥራ አምስት ቀናት በፊት ጉዞዬን ጀመርኩ። በመጀመሪያ ቶሮንቶን አልወደድኳትም ነበር፤ ከአንድ ወር በኃላ ተመልሼ ወደ ኢትዮጵያ ተመልስኩ ። የመኖሪያ ፈቃድ ይዞ ከ6 ወራት በላይ ከካናዳ ውጪ መኖር ስለማይፈቀድ በድጋሚ ወደ ቶሮንቶ መጥቼ ኑሮዬን እዚሁ አደረግኩ።

Image copyright Rebecca Teshome
አጭር የምስል መግለጫ የሐይቁ ዳርቻ

ቶሮንቶ 100 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ያሉባት ከተማ ናት። ሆኖም ዳንፎርዝ የተባለው አካባቢ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያን ያሉበት ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። የኢትዮጵያ ምግብ ቤቶች ፣የሽቀጣሸቀጥ መደብሮችና የተለያዩ አልባሳትም እንደልብ ይገኙበታል። የኢትዮጵያውያን ማዕከልም ያለበት ስለሆነ ሀገሬን በጣም ያስታውሰኛል። በየዓመቱ በዚሁ አካባቢ አዲስ ዓመትን በማስመልከት የ'ኢትዮጵያ ቀን' በአንድነት እናከብራለን።

ያለሁበት አካባቢ ከዋናው ከተማ ትንሽ ወጣ ያለ ስለሆነ ብዙ የሚታዩ ነገሮች ባይኖሩም በቶሮንቶ የሚያልፈው የኦንታሪዮ ሐይቅ ላይ ያለ የእግረኛ መራመጃ አለ። እኔም እዛ ዳርቻ ሄጄ በአግዳሚ ወንበር ላይ ቁጭ ብዬ መዝናናት ያስደስተኛል።

ኢትዮጵያንና ካናዳን በማነጻጽርበት ጊዜ ብዙ የሚያለያዩዋቸው ነገሮች ቢኖሩም ለእኔ ጎልቶ የሚታወቀኝ የካናዳ ማህበራዊ ደህንነት ነው። ምክንያቱም በአሁን ሰዓት የምሠራበት የሥራ መስክ ስለሆነ ሥርዓቱ ያስደንቀኛል። ሁሉንም ሰው የሚያካትተው የመኖሪያ ፣የሕክምና፣ የመዋለ ሕጻናትም ሆነ የትምህርት አቅርቦቱ በሰው የኑሮ ደረጃ የማይወሰን መሆኑ በጣም ልዩ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ።

Image copyright Rebecca Teshome
አጭር የምስል መግለጫ ከጓደኞችና ከቤተሰብ ጋር የሚደረጉ ቆይታዎች

ኑሮዬን በቶሮንቶ ከተማ ካደረግኩበት ጊዜ አንስቶ በጣም የሚያስደስቱ ገጠመኞችና ጊዜያትን አሳልፌያለሁ። ለምሳሌ በዚህ ከተማ ነው ያገባሁትም የወለድኩትም። ግን ከሁሉም በላይ ደግሞ ከዩኒቨርሲቲ የጨረስኩበት ስለሆነ በጣም ያስደስተኛል።

ቢሆንም ግን ኢትዮጵያ ትናፍቀኛለች። ከሁሉም በላይ በጣም የሚናፍቀኝ ደግሞ ሰው ተሰባስቦ፣ እጣን ተጫጭሶ በዓመት በዓል ጊዜ የምንገናኝባቸው ጊዜያት ናቸው። ለዚያም ነው በየአጋጣሚው ከቤተሰብና ከትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋር ለመሰባሰብ የምንሞክረው። በውጪውም ሆነ በሀገራችን ዓመት በዓል እያመካኘን እንሰባሰባለን። በዋነኝነት ድግሞ 'ቴንክስጊቪንግ' በተሰኘው በዓል ላይ የሀገርቤትም ሆነ የውጭ ምግቦችን እዘጋጅተን እንሰባሰባለን ።

እኔ የተለያዩ ምግቦችን ብወድም ለመሥራት የሚቀለኝ በብዛት የውጪውን ምግብ ነው። እንደ እንጀራ የሚሆንልኝ ምግብ ባይኖርም የሜድቴራንያንን ምግብ በጣም እወዳለሁ፤ ምክንያቱም ወደ ቅጠላቅጠሉ አደላለሁ። በቶሮንቶ ደግሞ የተለያዩ ሀገራት ምግብ ቤቶች ይገኛሉ፤ ለምሳሌ የጃማይካ፣ የግሪክ፣ የጣልያንና ብዙ ሌሎችም አሉ፤ ለእኔ ግን ሱፐር ሳላድ በቱና በጣም እወዳለሁ።

Image copyright Rebecca Teshome
አጭር የምስል መግለጫ 'ሱፐር ቱና ሳላድ'

ኢትዮጵያ እያለሁ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) በጥሩ ደምወዝ እሥራና ጥሩ ጓደኞች ስለነበሩኝ በማታ የትምህርት ክፍለ ጊዜ እየተማርኩ ብዙ የምፈልጋቸውን ነገሮችን አደርግ ነበር። በዛ ምክንያት እዚህ ስመጣ ትንሽ ለመላመድ ከበድ ብሎኝ ነበር። ከ28 ዓመታት በፊት ወደ ካናዳ ስመጣ ወረቀት ሰለነበረኝና ከራሴ ገንዘብ ውጪ ደግሞ የመንግሥትም ድጎማ ስለተጨመረልኝ ብዙም አልተቸገርኩም ነበር። ሥራም ለማግኘት ጥቂት ወራት ብቻ ነበር የፈጀብኝ። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ግን ከብደውኝ ነበር ። ከጊዜ በኃላ ግን እየለምድኩ ስመጣ ሁሉም ነገር ቀለለኝና ምንም ነገር ተቸግሬ አላውቅም።

ቶሮንቶ በጣም ቆንጆና የምትመች ከተማ ብትሆንም እንኳን የልጆቴ የወደፊት ሕይወት ያሳስበኛል። ምክንያቱም ብዙ ነገሮች የግል እየሆኑና ዋጋቸው እየናረ ነው። ከዚህ አንፃር ነው በተለይ የቤት ዋጋ ከወትሮ በተለየ መልኩ በጣም እየጨመረ መምጣቱ በጣም ያሳስበኛል፤ ለዚህም አቅሙ ቢኖረኝ ከቶሮንቶ አንድ መቀየር የምፈልገው ነገር ቢኖር የዋጋ ግሽበቱን ማስተካክል ነው።

በቅጽበት ኢትዮጵያ መሄድ ብችል ራሴን ማግኘት የምፈልገው ድሬዳዋ ነው ። ተወልጄ ያደግኩባት ስለሆነች ብቻ ሳይሆን የአኗኗር ዘይቤው ከአዲስ አበባ ይልቅ የተረጋጋና ዘና ያለ በመሆኑ ድሬዳዋ ምርጫዬ ናት።

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገረቻት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦

ካለሁበት 6 ''ከሀገር ቤት የስደት ኑሮዬ ይሻለኛል''

ካለሁበት 7፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ካምቦዲያ መኖር እፈልግ ነበር

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ