ሴባስትያን ኩርዝ፡ የኦስትሪያው ወግ አጥባቂ የዓለም ወጣቱ መሪ ሊሆን ነው

ሴባስቲያን ኩርዝ Image copyright Getty Images

በ31 ዓመቱ ሴባስትያን ኩርዝ የሚመራው የኦስትሪያው የወግ አጥባቂ ህዝቦች ፓርቲ በሀገሪቱ የተካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ እንደሚያሸንፍ ትንበያዎች ያሳያሉ።

ኩርዝም የዓለማችን ወጣቱ መሪ ለመባል ተቃርቧል።

ፓርቲው ከ31 በመቶ በላይ ድምጽ ሊያገኝ እንደሚችል እየተነገረ ነው።

አሁን የሚጠበቀው ደግሞ ከሶሻል ዲሞክራቶችና ከቀኝ ክንፍ የነጻነት ፓርቲ ሁለተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀውን መለየት ነው።

የኩርዝ ፓርቲ አሁንም ብቻውን መንግስት ለመመስረት የሚያበቃ አብላጫ ድምጽ ስላላገኘ "ከጸረ-ስደት" የነጻነት ፓርቲ ጋር ጥምረት ሊፈጥር ይችላል።

ሴባስቲያን ኩርዝ ማነው?

ኩርዝ ከአውሮፓውያኑ 2013 ጀምሮ በ27 ዓመቱ የኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን አገልግሏል።

ያኔም በአውሮፓ በእድሜ ትንሹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበር።

በግንቦት 2017 ደግሞ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነ።

የፖለቲካ እንቅስቃሴውን የጀመረው በፓርቲው የወጣቶች ክንፍ ሲሆን የቪየና ከተማ ምክር ቤትን እስኪቀላቀል ድረስም ሊቀ መንበር ነበር።

ያኔ '' በውሃ ላይ መራመድ የሚችል'' የሚል ቅጽል ስም ወጥቶለት ነበር።

ዋናው ጉዳይ ምንድን ነበር?

ኩርዝ ከ2015ቱ የአውሮፓ የስደተኞች ቀውስ ወዲህ ፓርቲው በይፋ የጸረ ስደተኛ አቋም እንዲኖረው አድርጓል።

በምርጫ ዘመቻው ወቅትም ዋነኛው አጀንዳ የስደተኞች ጉዳይ ነበር።

ወደ አውሮፓ የሚጓዙባቸውን መንገዶች እንደሚዘጋ፣ የመደጎሚያ ክፍያዎችን እንደሚያቆምና ቢያንስ ለ 5 ዓመታት በኦስትሪያ ካልቆዩ ምንም አይነት ጥቅማ ጥቅም እንደማያገኙ ለወግ አጥባቂና የቀኝ ክንፍ መራጮቹ ቃል ገብቶላቸዋል።

ተያያዥ ርዕሶች