የኢራቅ ሠራዊት የኩርድ ግዛቶችን እየተቆጣጠረ ነው

የኢራቅ ወታደሮች ወደ ኪርከክ ግዛት ሲያመሩ

የኢራቅ ሠራዊት በሰሜን ክፍል የምትገኘውን የኪርኩክ ከተማን ከኩርዲሽ አስተዳደር ነፃ አውጥቶ በቁጥጥሩ ስር ከማድረጉ ጋር ተያይዞ ግጭቱ ተጧጡፏል።

ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ መረጋጋት ሊሰፍን ይገባል ብላለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ-አቀባይ ሔዘር ኖውሬት ሁለቱም ወገኖች በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን ሊያስወግዱ ይገባል ብለዋል።

የኩርድ ክልላዊ መንግስት አነጋጋሪ የሚባለውን ከኢራቅ የመገንጠል ሕዝበ-ውሳኔ ያደረገው ከሦስት ሳምንታት በፊት ሲሆን፤ ይሄንንም ተከትሎ የኢራቅ ሠራዊት ግዛቱን በቁጥጥሩ ስር አውሏል ።

የኢራቅ ሠራዊት ተልዕኮ ኪርኩክን ብቻ ሳይሆን የእስላማዊ መንግሥት መመስረት ጋር ተያይዞ በኩርድ ቁጥጥር ሥር የወደቁ ግዛቶችን እንደገና የመመለስ አላማን አንግበዋል።

ኪርኩክን ጨምሮ በኩርድ ቁጥጥር ስር ውስጥ ያሉ ግዛቶች ከኢራቅ የመገንጠልን ሕዝበ-ዉሳኔን ደግፈዋል።

የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይደር አል አባዲ ሕዝበ-ውሳኔውን ህገ-መንግሥቱን ያልተከተለ ነው በማለት አውግዘውታል።

ነገር ግን የኩርድ ክልላዊ መንግሥት ህጋዊ ነው የሚል የአፀፋ ምላሽ ሰጥቷል።

እየተጋጋለ ባለው ቀውስ የአሜሪካ አቋም ምንድን ነው?

ሔዘር ኖውሬት ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ከኪርኩክ የሚሰሙ የግጭት ዜናዎች አሳሳቢ እንደሆነ ነው።

"ማዕከላዊውና ክልላዊው መንግሥት ተጣምረው የሚያስተዳድሩበትን ሰላማዊ ሥርዓት እንደግፋለን" ብለዋል።

ሔዘር ኖውሬት ጨምረውም ከሁለቱም ወገን የተውጣጡ የመንግሥት ባለስልጣናት መስማማት ላይ እንዲደርሱ አሜሪካ እየጣረች ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ባለስልጣናት ለማንም አይወግኑም ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የአሜሪካ ሴኔት የጦር ክፍል ኮሚቴን የሚመሩት ጆን ማኬይን በበኩላቸው አሜሪካ የምትለግሳትን የጦር መሳሪያ ኢራቅ ለዚህ ግጭት ብታውለው የከፋ ነገር እንደሚገጥማት አስጠንቅቀዋል።

"የአሜሪካ መንግሥት ለኢራቅ የጦር መሳሪያ የለገሰው ከእስላማዊ መንግሥት እንዲሁም ከውጭ ጠላቶች ለመከላከል እንጂ የራሷን ግዛቶች ለማጥቃት አይደለም" ብለዋል።

የባግዳድና የኩርድ ባለስልጣናትስ?

የኢራቁ ፕሬዚዳንት አባዲ ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ ኪርኩክ ላይ የተደረገው ወታደራዊ እርምጃ በሕዝበ-ውሳኔው ምክንያት የመከፋፈል አደጋ ለተጋረጠባት ኢራቅ የአገሪቱን አንድነት ከማስከበር አንፃር አስፈላጊ ነው።

የኢራቅ ሠራዊት ባባ ጉርጉር የዘይትና የነደጅ ማምረቻ ቦታን በቁጥጥር እንዳዋለ ተናግሯል።

ምንም እንኳን የኢራቅ ባለስልጣናት የኩርድ ወታደሮች ያፈገፈጉት ያለ ጦርነት ነው ቢሉም የጥይት ድምፆችና ግጭት እንደነበረ በቢሲ የተቀረፀ ቪዲዮ ያሳያል።

ግጭቱንም ፍራቻ በሺዎች የሚቆጠሩ የግዛቱ ነዋሪዎች በመሰደድ ላይ ናቸው።

የኢራቅ ሠራዊት የኪርኩክ ግዛቶችን ሙሉ በሙሉ እየተቆጣጠረ መሆኑን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ።

ሁለቱ አካላት በሚጋጩባቸው በነዚህ ግዛቶችም የኢራቁ ፕሬዚዳንት አባዲ ሰንደቅ አላማ እንዲዉለበለብም አዘዋል።

የኢራቅ ሠራዊት የኪርኩክ ግዛትን የተቆጣጠረበት ፍጥነት፤ የኩርድ ሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች እርስ በርሳቸው መረጃን አሳልፎ በመስጠትና በክህደት ምክንያት እንዲወነጃጀሉ አድርጓቸዋል።

በተያያዘ ዜና የቱርክ መንግሥት በኢራቅ የተከሰተው የኩርድ የነፃነት ጥያቄ በቱርክ ለሚኖሩት ኩርዶች ተመሳሳይ መንገድ ይከፍታል በሚል ፍራቻ የኢራቅን ወታደራዊ ተልዕኮ አወድሷል።

የኩርድ የሠራተኞች ፓርቲ ከቱርክ ተገንጥሎ ራስ ገዝ አስተዳደርን ለመመስረት ከሦስት አስርት አመታት በላይ ታግሏል።

ይህ ቡድን በቱርክ፣ በአውሮፓ ህብረት እንዲሁም በአሜሪካ በአሸባሪነት ይወነጀላል።

ኪርክ የቀውሱ ማዕከል ለምን ሆነች?

ኪርኩክ በተፈጥሮ ጋዝ የበለፀገች ስትሆን፤ ከዚሁም ጋር ተያይዞ በኩርድ እና በማዕከላዊው መንግሥት መካከል የይገባኛል ጥያቄ ምክንያት የግጭቶች መነሻም ናት።

በዋናነት የኩርድ ሕዝብ መቀመጫ ስትሆን ዋና ከተማዋ የአረብና ቱርካዊያን ነዋሪዎች በብዛት አሉባት።

ከእስላማዊ መንግሥት መመስረትና ከኢራቅ መዳከም ጋር ተያይዞ ለሦስት ዓመታት በኩርዶች አስተዳደር ሥር ነበረች።