ካይሮ ለሴቶች በጣም አደገኛ ከሆኑች ከተሞች አንዷ ናት - ጥናት

ካይሮ
አጭር የምስል መግለጫ ከተማው ለሴቶች አስቸጋሪ ነው

የግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ ለሴቶች "በጣም አደገኛ" ከሆኑ ትልልቅ ከተሞች አንዷ መሆኗ ተገልጸ።

ከ10 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ባሏቸው ከተሞች፤ የሴቶችን ሁኔታ በሚመለከት የተካሄደው የመጀመሪያው ዓለም አቀፋዊ የሕዝብ አስተያየት ጥናት ነው ይህንን የገለጸው።

ጥናቱ በህዝብ ብዛታቸው ትልልቅ በሆኑ 19 ከተሞች ሴቶች ምን ያህል ከወሲብ ጥቃቶች እንደተጠበቁ በሚያመለክቱ ጉዳዮች ላይ የሥነ-ጾታ ባለሙያዎችን በመጠየቅ የተካሄደው ነው።

በምርጫው ለንደን ቀዳሚውን ቦታ ስትይዝ ቶክዮ እና ፓሪስ ተከታዮች ሆነዋል።

ሴቶች ሥነ-ጥበብ፣ ንግድ እና ፖለቲካን ጨምሮ በሁሉም የማህበራዊ ክፍሎች ቀዳሚ በመሆን እየመሩ ናቸው ሲሉ የለንደን ከተማ ከንቲባ ሳዲቅ ካን ገልጸዋል።

በካይሮ የሚገኙ የሴቶች መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ለመቶ ዓመታት የቆዩ ልምዶች፤ መድልዎ እንዲኖር ከማድረጋቸውም በላይ ሴቶችን ለመርዳት የሚወሰዱ እርምጃዎችን አዝጋሚ አድርገውታል።

በተጨማሪም በቂ የጤና እንክብካቤ፣ የገንዘብ እና የትምህርት ተደራሽነት አያገኙም።

ግብጻዊቷ ጋዜጠኛ ሻሂራ አሚን ከተማዋ ለሴቶች አስቸጋሪ ናት ትላለች። በመንገድ ላይ እንደ መራመድ ያሉ ቀላል ነገሮችም ሴቶችን ለውክቢያ እና መንገላታት ሊያጋልጡ ይችላል ብላለች።

በቶማስ ሮይተርስ ፋውንዴሽን የተደረገው ጥናት የፓኪስታኗ ካራቺ፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክዋ ኪንሻሳ እና የሕንዷ ዴልሂ ያገኙት ውጤት ከካይሮ ኋላ አስቀምጧቸዋል።

ዴልሂ እና የብራዚሏ ሳኦ ፓውሎ ሴቶች ወሲባዊ ትንኮሳ፣ ወሲባዊ ጥቃት እና አስገድዶ የመድፈር ስጋት ከፍተኛ ከሆነባቸው ከተሞች ቀዳሚ ሆነዋል።

እ.አ.አ በ2012 በአውቶብስ ውስጥ የተደፈረችን ሴት ምክንያት በማድረግ ከነበረው ከፍተኛ ተቃውሞ በኋላ ጠንካራ ህግ ቢወጣም ዴልሂ በዝርዝር ውስጥ ገብታለች።

በብራዚል 16 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆናቸው ሦስት ሴቶች ውስጥ አንዷ አካላዊ፣ የንግግር ወይንም የሥነ-ልቦና ጥቃት እንደሚደርስባት የብራዚል ፎረም ኦፍ ፐብሊክ ሴክዩሪቲ ያካሄደው የህዝብ አስተያየት ጥናት ይፋ አድርጓል።