የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጉባኤ በቤጂንግ ተጀምሯል

የፓርቲው አባላት በመቀመጫቸው Image copyright Reuters

በቻይና ከፍተኛው የፖለቲካ ውሳኔ የሚተለለፍበት የኮሚኒስት ፓርቲ ጉባኤ ከከፍተኛ የደህንነት ጥበቃ ጋር በቤጂንግ ተጀምሯል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ከ 2000 በላይ ለሚሆኑት ተወካዮች ለሶስት ሰዓታት የፈጀ ንግግር አድርገዋል።

በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው ዝግ ጉባኤ የቻይናን ቀጣይ መሪና የወደፊት አቅጣጫዎች ይወስናል።

ዢ በንግግራቸው ''ሶሻሊዝም ከቻይና ባህሪ ጋር ተዳምሮ አሁን የዓለማችን ልዕለ ኃያል ሆናለች ''ብለዋል።

ሀገራቸው የውጪ የፖለቲካ ስርዓትን ግልባጭ እንደማትወስድም ተናግረዋል።

ተጨማሪ የኢኮኖሚያዊ መሻሻሎች እንደሚኖሩና ቻይና ለዓለም በሯን የመዝጋት እቅድ እንደሌላት ጠቁመዋል።

ለዚህም በውጭ ባለሃብቶች ዙሪያ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመቀነስ ቃል ገብተዋል።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ በአውሮፓውያኑ 2012 ፕሬዝዳንት የሆኑት ዢ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል

የቻይናን የቀጣይ አምስት ዓመት ፍኖተ ካርታም የሚወስነው ይህ ጉባኤ በቀጣዩ ሳምንት ይጠናቀቃል።

ከጉባዔው በኋላም የቻይና ከፍተኛ ውሳኔ ሰጪ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ይፋ ይደረጋሉ።

ቤጅንግም የጉባኤውን መጀመር በሚያሳዩ ምልክቶችና ማስጌጫዎች ደምቃለች።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ዜጎችም ከጉባኤው ማስጌጫዎች ጋር ፎቶግራፍ እየተነሱ ነው

የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ፓርቲው ህግ መንግስቱንም እንደአዲስ እንደሚያረቅ ዘግበዋል።

ፓርቲው የዢን የስራ ሪፖርትና ፖለቲካዊ ኃሳቦችን በማካተት ከቀድሞዎቹ የፓርቲው ልሂቃን ማኦ ዜዶንግና ዴንግ ዢያኦፒንግ ጋር እንዲስተካከሉ የማድረግ እቅድ ይዘዋል።

ፕሬዝዳንት ከሆኑ ወዲህ ዢ ቅድመ ምርመራን በመተግበር እንዲሁም የህግ ጠበቃዎችንና የፖለቲካ አቀንቃኞችን በማሰር በቻይና ፖለቲካም ሆነ በፓርቲው ከፍተኛ ቁጥጥር ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በአንጻሩ ደግሞ የቻይና ስልጣኔና የኦኮኖሚ ማሻሻያዎች በፍጥነት እየገሰገሱ በዓለምአቀፍ መድረክም እየተሰመከረላቸው ነው።

በቻይና ህዝብም ዘንድ ያላቸው ከፍተኛ ተቀባይነትም እንደቀጠለ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች