ትራምፕ ለመጨረሻ ጊዜ ይፋ ያደረጉት የጉዞ ዕገዳ ውድቅ ተደረገባቸው

A woman (middle) travelling from Jordan on a Yemeni passport arrives in Los Angeles, California Image copyright Reuters

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለመጨረሻ ጊዜ ያፀደቁት ከስምንት ሃገራት የሚመጡ ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያግደው ዕቅድ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል።

በዚህ ሳምንት ተግባራዊ እንደሚደረግ ሲጠበቅ የነበረው የጉዞ ዕገዳ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲይ አንድ የአሜሪካ ፌዴራል ዳኛ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ዕቅዱ ከኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣ ሶማሊያ፣ ቻድ እና ሰሜን ኮሪያ የሚመጡ ዜጎች እንዲሁም አንዳድንድ የቬንዚዌላ ባልስልጣናት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያግድ ነው።

ትራምፕ ስልጣን ከያዙ ወዲህ ይህ ሦስተኛው መሰል ዕገዳ ሲሆን የመጀመሪያው ዕገዳ በብዛት ሙስሊሞች የሚገኙባቸው ሃገራት ላይ ያተኮረ በመሆኑ "የሙስሊም ዕገዳ" እየተባለ ሲጠራ ይሰማል።

የአሜሪካዋ ሃዋይ ግዛት የትራምፕን ዕቅድ ውድቅ በማድረግ በዕለተ ረቡዕ ተግባራዊ ሊደረግ የነበረውን ፖሊሲ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም አድርጋለች።

ትራምፕ ከምርጫ በፊት "ሙስሊሞች ወደ ሃገሬ እንዳይገቡ ሙሉ በሙሉ አግዳለሁ" በማለት የተናገሩትን በዚህ ዕገዳ አማካይነት እየተገበሩት ነው ሲሉ የግዛቲቱ ሰዎች ተከራክረዋል።

በተጨማሪም በፌዴራል ስደኞች ሕግ መሠረት ፕሬዝዳንቱ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን የማስተላለፍ ስልጣን የላቸውም ሲሉ የሁዋይ ግዛት ሰዎች ጉዳዩን ለፍርድ ቤት አቅርብዋል።

ያለፈውን የትራምፕ ዕገዳ ውድቅ ያደረጉት የአሜሪካ ፌዴራል ዳኛ ዴሪክ ዋትሰን በድጋሚ አዲሱን ረቂቅ ተቀባይነት እንዳያገኝ አድርገውታል።

"የትራምፕ ዕቅድ ከባለፈው ጋር በተመሳሳይ መልኩ ችግር ይታይበታል" ሲሉ ዳኛ ዋትሰን ተናግረዋል።

"የእነኚህ ሰዎች ወደ አሜሪካ መምጣት በሃገሪቱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምን እንደሆነ በግልፅ ማሳየት ያልቻለ ፖሊሲ" በማለት ውድቅ ያደረጉበትን ምክንያት አስረድተዋል።

ዕቅዱ በተመሳሳይ ከሜሪላንድ፣ ዋሽንግተን፣ ማሳቹሴትስ፣ ካሊፎርኒያ፣ ኦሪገን እንዲሁም ኒው ዮርክ ግዛቶች ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል።

የዋይት ሃውስ ፕሬስ ፀሓፊ ሳራ ሳንደርስ ለሚድያ ስለጉዳዩ እንደተናገሩት "ዕገዳው እንዳይተገበር ማድረግ አሜሪካውያን ደህንነታቸው እንዳይጠበቅ ማድረግ ነው" ብለዋል።

''የፕሬዚደንቱ ዕቅድ ወጣም ወረደ በግዛቶች ድጋፍ አግኝቶ መተግበሩ አይቀርም" ሲሉ አክለዋል ሳራ።

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህ ሦስተኛው ዕገዳ ከመጀመሪያው እና ሁለተኛው የሚለይበትን ዝርዝር መግለጫ እንዲያቀርቡ ለሁሉም ፓርቲዎች ትዕዛዝ አስተላለፏል።