ክሴንያ ሶብቾክ ለፕሬዝዳንትነት እንደምትወዳደር ይፋ አድርጋለች

ሶብቾክ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ሶብቾክ እጩ የሆንኩት ያንን የማድረግ እድል ለሌላቸው ሰዎች ድምጽ ለመሆን ነው ብላለች

ሩሲያዊቷ ክሴንያ ሶብቾክ ቭላድሚር ፑቲን እንደሚሳተፉበት በሚጠበቀው የመጪው መጋቢት ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደምትወዳደር ይፋ አድርጋለች።

ሶብቾክ ራሷን እጩ ከማድረጓ በፊት ለተቃዋሚው መሪ አልክሲ ናቫልኒ ድጋፍ ስትሰጥ የነበረ ቢሆንም እርሱ ከመወዳደር ሲታገድ በእግሩ ተተክታለች።

ነገር ግን እርሱም እንዳትወዳደር አስጠንቅቋት ነበር።

በዚህም የተነሳ እንዳንድ ተንታኞች በተቃዋሚዎች መካከል መከፋፈል እንደሚፈጥር እየተነበዩ ነው።

ክሬምሊን ግን እጩነቷን ሙሉ በሙሉ ህገመንግስታዊ ነው በሚል ተቀብሎታል።

ናቫልኒ አሁን ተቃውሞ በማዘጋጀት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ በ20 ቀናት አስር ላይ ነው።

በምርጫውም እንዳይወዳደር እገዳ ተጥሎበታል።

ናቫልኒ ግን ሆን ተብሎ የተፈጠር የሃሰት ወሬ ነው ባይ ነው።

አሌክሲ ናቫልኒ ባለፈው ወር ከመታሰሩ በፊት ክሴኒያ ሶብቾክ የክሬምሊን "አዝናኝ"እንጂ ፕሬዝዳንት መሆን አትችልም በሚል እጩነቷን ሳይቀበለው ቀርቷል።

''ለለዝብተኞች የቀልድ መዝገብ ፣ለተቃዋሚዎች ደግሞ ትርጉም አልባ ምርጫ ህጋዊ እውቅና ለመስጠት የተጨመረች አስቂኝና የተጋነነች ምስል" ሲል ተሳልቆባታል።

''እንዲያውም በማህበራዊ ሚዲያ ተጨማሪ ወዳጆችና ተከታዮች ለማፍራት የምታልም አርቲስት'' ብሏታል።

ሶብቾክ ግን ምንም አይነት ጉዳት የማድረስ አላማ እንደሌላትና ናቫልኒ እንዲወዳደር ከተፈቀደለት ራሷን ከእጩነት እንደምታነሳ ተናግራለች።

ነገር ግን ይህ እውን የመሆኑ እድል በጣም ዝቅተኛ ነው።

Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ናቫልኒ በብዙዎች የፑቲን የፖለቲካ ተቀናቃኝ ተደርገው ይወሰዳሉ

ጋዜጠኛ የነበረችውና የማህበራዊ ፍትህ አቀንቃኝ የሆነችው ሶብቾክ በመሪዎቻቸው የውሰጥ ወሬ፣ ልብነትና ሙስና ለተማረሩ ዜጎች ድምጽ እንደምትሆን ቃል ገብታለች።

በሩሲያም በ 14 ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት እጩ ሆናለች።

የምርጫው ዘመቻም የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ በማካሄድ እጩዎቻቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ በታህሳስ ይጀመራል።

በሩሲያ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ እጩ በገለልተኛነት ለመወዳደር የሚጠበቅበት 300 ሺህ ድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2000 ጀምሮ ወደ ሥልጣን የመጡት ፑቲን እስለካሁን በምርጫው እንደሚወዳደሩ አላሳወቁም።

ሴንያ ሶብቾክ ማን ናት?

  • የ35 ዓመቷ እጩ በ1990ዎቹ የአሁኑን መሪ ቭላድሚር ፑቲንን ለሩሲያ የስለላ ድርጅት(ኬ ጂ ቢ) የቀጠሩት የቀድሞው የቅዱስ ፒተርሰበርግ ከንቲባ አናቶሌ ሶብቾክ ልጅ ናት።
  • ፍቅረኞችን በሚያገናኝ የቴሌቪዥን ዝግጅት በማቅረብ አድናቆትን አትርፋለች።
  • በአረፋ ከተሞላ የመታጠቢያ ቤት ገንዳ ሆና በምታቀርበው ሌላ የቴሌቪዥን ዝግጅትም ትኩረትን ስባ ነበር።
  • ከ2012 ጀምሮ ደግሞ ፑቲንን በመቃወም የተቃዋሚ ፓርቲ ድጋፍ መስጠት ጀምራለች።