የሴቶች ብቻ መጓጓዣዎች ደህንነትን ያረጋጋግጣሉ?

የኬንያ አውቶብስ Image copyright Getty Images

በኬንያ 'ማታቱ' ተብለው የሚጠሩት የህዝብ ማመላለሻዎች በናይሮቢ ጎዳናዎች ለይ በቀላሉ እይታ ውስጥ ይገባሉ።

ከከተማዋ 3 ሚሊዮን ነዋሪዎች ብዙኃኑ ለመጓጓዣ የሚመርጡት እነዚህን አውቶብሶች ነው።

ለብዙ ሴቶች ግን አውቶብሱ የጾታዊ ትንኮሳና ጥቃት መፈጸሚያ ቦታ ነው።

ሊን ባራዛ እህቷን አውቶብስ መሳፈሪያ ቦታ ልታደርስ በሄደችበት አጋጣሚ ነበር የ'ማታቱ' አሸከርካሪዎች በቡድን ሆነው ሁለቱም ወደ መኪናው ውስጥ እንዲገቡ ያስገደዷቸው።

''ሁለታቻንንም መግፋት ጀመሩ፤ ልጇን አቅፋ የነበረችውን እህቴንም እጇን መጎተት ጀመሩ" በማለት ትውስታዋን ታጋራለች።

''ጾታን መሰረት ያደረገ አጸያፊ ቃላትን ሲናገሩ ነበር፤ እኔም ብቻችንን እንዲተዉን ነገርኳቸው። ማንም እንደማይረዳን ስረዳ ግን አለሰቅኩኝ፤ እህቴም በጣም ፈርታ ነበር'

በእርግጥ ሊንና እህቷ የአካል ጉዳት አልደረሰባቸውም፤ ይህ ገጠመኛቸው ብዙ ሴቶች በየቀኑ የሚኖሩት ህይወት ነው።

በናይሮቢ የመብት ተቆርቋሪ ቡድን በተደረገ ጥናት ከተካተቱ ሴቶች ብዙዎቹ በህዝብ መጓጓዣዎች ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ተጎጂዎች ሆነው ተገኝተዋል።

ይህ ችግር በአንድ ቦታ ላይ የሚወሰን አይደለም።

በፓሪስ የጎዳና ላይ ትንኮሳ ይቁም በሚባል ድርጅት የተደረገው ሌላ ጥናትም ተመሳሳይ ውጤት አሳይቷል።

በከተማዋ የህዝብ ትራንስፖርት የሚጠቀሙ ሴቶች መቶ በመቶው ቢያንስ አንድ ጊዜ ትንኮሳ ደርሶባቸዋል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በጃፓን የሴቶች ብቻ መጓጓዣዎች ተዘጋጅተዋል ፤ ግን የጉዞ ደህንነትን ያረጋግጣሉ?

ሴቶችን ብቻ የሚያሳፍሩ መጓጓዣዎች ሲኖሩስ?

አንዳንድ ፖለቲከኞች ለዚህ ችግር እንደመፍትሄ የሚወሰዱት ሴቶችን ብቻ የሚይዝ መጓጓዣን ማዘጋጀት ነው።

በሜክሲኮ፣ ጃፓንና ህንድ በአውቶብስ በባቡርና በታክሲዎች ተሞክረው ታይተዋል።

ነገር ግን ይህ እርምጃ የሴቶችን ደህንነት እንደሚያረጋገጥ የሚያሳይ ማስረጃ አለ?

ይህንን መመዘን በብዙ ምክንያቶች አስቸጋሪ ይሆናል።

በህዝብ መጓጓዣዎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች አብዛኛዎቹ ሪፖርት አይደረጉም፤ ቢደረጉም ብዙ ሀገራት መረጃውን ይፋ አያደርጉትም።

ምንም እንኳን የመጓጓዣ አገልግሎቱን የመለየት ሁኔታ በሌሎች ምክንያቶችም ሊመጣ ቢችልም፤ ብዙዎቹ ሀገራት ግን የሴቶችን ማጓጓዣን ያስተዋወቁት አስቀድሞም የጾታ ትንኮሳ ችግር ስለነበረባቸው ነው።

እናም ይህን የሴቶች ማጓጓዣ ከማዘጋጀታቸው በፊት ከዚህ የበለጠ አደገኛ የነበሩ ከተሞች ሊሆኑ ይችላሉ።

ይህን ማረጋጥ የሚቻለው ደግሞ መጓጓዣውን መጠቀም ከመጀመራቸው በፊትና በኋላ ያለውን ሁኔታ በማነጻጸር ነው።

ይህንን ለማድረግ የሚያግዝ መረጃ ያላቸው ሀገራት ግን በጣም ጥቂት ናቸው።

ይህ መረጃ በአግባቡ ከሚገኝባቸው ቦታዎች አንዷ ቶኪዮ ነች።

ቶኪዮ ከአውሮፓውያኑ 2004 ጀምሮ በበርካታ የባቡር መስመሮች ሴቶችን ብቻ የሚያጓጓዝ ክፍል አስተዋውቃለች።

አገልግሎቱ ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላም በከተማዋ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ያልተገቡ ባህሪያት ሪፖርቶች በ3 በመቶ ቀንሰዋል።

ሆኖም የሴቶች ብቻ መጓጓዣዎች ከተዘጋጁባቸው መስመሮች በሁለቱ የትንኮሳ ሪፖርቶች ከ15 -20 በመቶ ጨምሮ ተገኝቷል።

ይህ ሊሆን የቻለው ወንዶችና ሴቶች ተቀላቅለው በሚጓዙባቸው መጓጓዣዎች የሚፈጸሙ ትንኮሳዎች ስለበዙ ወይም ሪፖርት የሚያደርጉት ሴቶች ስለጨመሩ ሊሆን ይችላል።

በእርግጥ በርካታ ሴቶች፤ ወንዶች በሌሉበት ሲጓዙ ደህንነት እንደሚሰማቸው ይታወቃል።

ሮይተርስ በ2014 በመላው ዓለም በ6300 ሴቶች ላይ ባካሄደው ጥናት 70 በመቶ የሚሆኑት በተለየ መጓጓዟ መሳፈርን እንደሚመርጡ አረጋግጧል።

ሆኖም በውጤቱ የአንዱ ሀገር ከሌላኛው አንፃር ከፍተኛ ልዩነት ታይቶበታል።

በፊሊፒንሷ ማኒላ ከተማ ለሴቶች ብቻ በተዘጋጀ ትራንስፖርት መጓዝ የሚፈልጉት 92 በመቶ ሲሆኑ በኒውዮርክ ግን 35 በመቶ ብቻ ናቸው።

በጥናቱ ለሴት ተጓዦች በጣም አደገኛ የሆኑ 16 የዓለማችን ትላልቅ ከተሞች በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል።

ከመጀመሪያዎቹ አምስት ከተሞች አራቱ ማለትም የኮሎምቢያዋ ቦጎታ፣ የህንዷ ዴልሂ፣ የኢኖዶኔዢያዋ ጃካርታና የሜክሲኮዋ ሜክሲኮ ሲቲ የሴቶች ብቻ መጓጓዣን በተወሰነ መልኩ እየተገበሩ ያሉ ናቸው።

ስለዚህ ሴቶች በዚህ መልኩ መንገዳችን የተሻለ ይሆናል ብለው ቢያስቡም እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው።

Image copyright Lynn Baraza
አጭር የምስል መግለጫ ሊን ባራዛ '' ማንም እንደማይረዳን አወቅኩ''

ፈጣኑ ማስተካከያ

ግን ሴቶች ብቻቸውን ሲጓዙ ደህንነት የሚሰማቸው ከሆን ይህንኑ ማስተዋወቅ አይሻልም?

ምንም እንኳን ችግሩ ቢደርስባትም ሊን ይህ መፍትሄ እንደሚሆን አታስብም።

ይልቁንም ማህበረሰቡን ለመለወጥ የሚቻለው ለየትኛውም ትንኮሳ ምንም አይነት ትዕግስት እንዳይኖረው በማስተማር ነው ትላለች።

ደግሞም ሴቶቹ በጉዞ ወቅት ደህንነታቸው ቢጠበቅም ከአውቶብሱ ከወረዱ በኋካ ግን ትንኮሳው ይቀጥላል፤ እንዲያውም ሊባባስ ይችላል ባይ ናት።

ሊን ብቻ አይደለችም የዚህ ፖሊሲ ዕይታ የተዛባ ነው ብላ የምታስበው።

በርካታ ምሁራንና ፖሊሲ አውጪዎች የተነጠሉ የመጓጓዣ መንገዶችን ማዘጋጀት የሴቶችን ጥቃት እውቅና የመስጠት ያህል ነው ይላሉ።

ይህ እርምጃ የጥቃት ፈጻሚዎቹን ባህሪ ከመለወጥና ውጤታማ የህግ ማዕቀፎችን ከማውጣት ይልቅ ሴቶች ጥቃትን እንዲሸሹ ያደርጋል በሚል ይሞግታሉ።