ብክለት የዓለምን ድሃ ህዝብ እየጨረሰ ነው?

አፏን የሸፈነች ሴት Image copyright Getty Images

በአውሮፓውያኑ 2015 ከአካባቢ ብክለት ጋር በተያያዘ ምክንያት 9 ሚሊዮን ሰዎች እንደሞቱ 'ዘ ላነሴት ' የተባለው የጤና መጽሄት ባወጣው ሪፖርት አረጋግጧል።

እነዚህ ሞቶች ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ የተከሰቱት አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሃገራት ነው።

በሀገራቱ ከሚመዘገቡት ሞቶች የአካባቢ ብክለት እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል።

ባንግላዴሽና ሶማሊያ ደግሞ ሁኔታው ከሁሉም ቦታ የተባባሰባቸው ሀገራት ናቸው።

የአየር ብክለት፤ ከብክለት ጋር ከሚያያዙ ሞቶች 2/3ኛውን በመሸፈን ከፍተኛ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው።

ከእነዚህ ሞቶች መካከል ብዙዎቹ የተከሰቱት በልብ በሽታ፤ በእዕምሮ የደም ዝውውር ማቆም( ስትሮክ) እና የሳንባ ካንሰር በሽታዎች ነው።

ብሩናይ እና ስዊድን ደግሞ ከብክለት ጋር የተያያዘ ሞት መጠን አነስተኛ የሆነባቸው ሀገራት ሆነዋል።

'' ብክለት አሁን ለአካባባቢ ፈተና ሆኗል፤ በጣም እየተስፋፋ ያለና ከባድ የሰው ልጅ የጤናና ደህንንነት ስጋት ነው።'' ይላሉ የጥናቱ ፀሃፊ ፊሊፕ ላንድሪጋን።

Image copyright SAJJAD HUSSAIN

ከእነዚህ ዋነኛው ስጋት የሆነው የአየር ብክለት የ6.5 ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት በአጭሩ ይቀጫል።

ይሄ ደግሞ በቤት ውስጥ እንጨት በማንደድና በከሰል ምክንያት፣ ከውጪ ደግሞ በጋዝ ልቀት የሚከሰት ነው።

በሚከተለው የውሃ ብክለት ደግሞ 1.8 ሚሊዮን ሰዎችን ሲሞቱ ከእነዚህ 800,000 የሚሆኑት የሞቱት ከሥራ ቦታ ጋር በተያያዘ ብክለት ነው።

ከሞቱት 92% የሚሆነው የተከሰተው በድሀ ሃገራት ሲሆን፤ ችግሩ የተባባሳው ደግሞ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ልማት እየሰሩ ባሉት ሃገራት ነው።

በተመዘገበው ሞት ብዛት ደረጃም ህንድ አምስተኛ፣ ቻይና ደግሞ አስራ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም ከተመዘገቡ 50,000 ሞቶች 8% የሚሆነው በብክለት ምክንያት የተከሰተ ነው። ይህም ከ188 ሀገራት 55ኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል።

በብሪታንያ የሳንባ ተቋም የሚሰሩት ዶክተር ፔኒ ዉድስ እንደሚሉት በዩናይትድ ኪንግደም ከምዕራብ አውሮፓ ሀገራትም ሆነ ከአሜሪካ በላይ ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል

'' ምናልባትም መርዛማ ጭስና ንጥረ ነገሮችን ወደ አየር በሚለቁ የነዳጅ መኪኖች ላይ ጥገኛ መሆናችን በተለይም ህጻናትና አዛውንቶችን ለሳንባ በሽታ እያጋለጣቸው ነው'' ብለዋል።

Image copyright Peter Macdiarmid

በአሜሪካ ደግሞ 5.8% ማለትም የ155,000 ሰዎች ሞት ከብክለት ጋር የተገናኘ ሆኗል።

ፀሃፍቱ እንደሚገልጹት የአየር ብክለት የድሃ ሀገራት ህዝቦችና በበለጸጉ ሀገራት የሚገኙ ድሆችን ክፉኛ እያጠቃ ነው።

እናም ብክለት በዘመናችን በህይወት የመኖር፣ የጤና ፣ የደህንነት እንዲሁም የህጻናትና ሌሎች ተጋላጭ ሰዎች ክብካቤ ማግኘትን የመሰሉ መሰረታዊ መብቶችን አደጋ ላይ ጥሏል።