የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በሴቶች ላይ ችግር አለበት?

ሴቶች በፓርላማ Image copyright AFP

ፕሬዝዳንት ዢ በ19ኛው የኮሚኒስት ፓርቲ ጉባዔ ላይ ንግግራቸውን ሲያሰሙ 2,280 ተወካዮች አንገታቸውን ቀና አድረገው ይከታተሏቸዋል።

ከእነዚህ ሰዎች ግን ሴቶች ወደ 25 በመቶ የሚጠጉት ብቻ ናቸው። በዚህ ምክንያት ነው አንዳንድ ሰዎች ፓርቲው የጾታ እኩልነትን ከዚህም በላይ ሊያስብበት ይገባል የሚሉት።

ኒውዮርክ ታይምስ ሴቶቹ ድምጽ አልባ ናቸው ይላል። እውን የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሴቶች ላይ ችግር አለበት?

ከፓርቲው 89.4 ሚሊዮን አባላት 26 በመቶው ማለትም 23 ሚሊዮኑ ሴቶች ናቸው። በፖለቲካው ወደ ላይ ከፍ እያለ ሲመጣ ደግሞ ሴቶች ብዙም ውክልና የላቸውም።

ባለፈው የ2012 የፓርቲው ጉባዔ በሀገሪቱ ዋነኛ ጉዳዮችን የሚወስነውን ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሚመርጠው ቡድን ከአጠቃላዩ 9 በመቶውን የሚሸፍኑ 33 ሴት አባላት ብቻ ነበሩት።

በቋሚ ኮሚቴው አባልነት የተመሩት ሴቶች ደግሞ 8 በመቶ የሚሆኑት 22 አባላት ብቻ ነበሩ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ከጉባዔው ተወካዮች 25 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው

በእርግጥ ሴቶች በቻይና ፖለቲካ ሰብሮ መግባት እንደሚከብዳቸው ይታወቃል።

ይህ የሚሆነው ደግሞ የሀገሪቱ መንግስት የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆኑን በሚገልጽበት፣ ከወንዶች ይልቅ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ሴቶች በሚበዙባት ቻይና ነው።

ታዲያ ወደኋላ የሚጎትታቸው ምንድን ነው?

ሴቶች ብዙ ጊዜ ፓርቲውን የሚቀላቀሉት እንደአንድ ራሳቸውን የማሳደጊያ መንገድ በዩኒቨርሲቲ ወይም በሥራ ቦታ ነው።

ሆኖም ከግዛትና ከከተሞች የዘለለ ዕድገት ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው።

"የሴቶች ቦታ በቤት ውስጥና በማዕድ ቤት ነው የሚለው ለረጅም ጊዜ የቆየው አመለካከት የተሻለ ህይወት እንዳያስቡ ይጎትታቸዋል'' ይላሉ በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሊኒት ሆንግ።

እናም " ማሕበራዊ ሚናቸው ባላቸውን፣ ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን መንከባከብ ሆኗል''

ምንም እንኳ ''ሴቶች የሰማይ ግማሹን ይይዛሉ'' የሚለውን የማኦ ንግግር ብዙዎች ቢያውቁትም አሁንም ቢሆን እኩል ውክልና ለመፍጠር ገና ብዙ መጓዝ ይጠይቃቸዋል።

Image copyright Reuters

የሴቶች ጡረታ መውጫ እድሜ ዝቅ ማለቱም የዕድገት ዕድሎችን ያጠባል። በመንግሥት መሥሪያ ቤትና የልማት ድርጅቶች ሴቶች ጡረታ የሚወጡት በ55 ዓመታቸው ሲሆን ወንዶች ደግሞ በ60 ዓመታቸው ነው።

በሌሎች ድርጅቶች የሚሰሩ ሴቶች የጡረታ እድሜ ደግሞ 50 ነው። ግን የቻይና ሁኔታ ከሌሎች ይለያል? የቻይና ሴቶችስ ከሌላው ዓለም በተለየ ተጎድተዋል?

መረጃዎች የሚያመለክቱት በሌላውም ሀገር እንዲሁ መሆኑን ነው፤ በዓለማችን ውሳኔ ሰጪ አካላት የሴቶች ድርሻ አነስተኛ ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም የታችኛው ምክር ቤት ሴት አባላት 32 በመቶ ናቸው። ይህ ከእስካሁኑ ጊዜ ከፍተኛው ነው።

ሴቶች በህንድ 11 በመቶ፣ በጃፓን ደግሞ 9 በመቶ ብቻ የፓርላማ ቦታ አላቸው።

ሆኖም ከዚህ በጣም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ሀገራት አሉ።

በሩዋንዳ 61 በመቶ፣ በኩባ ደግሞ 49 በመቶ የሚሆኑት ወንበሮች በሴቶች ተይዘዋል።

በብራዚል ሳኦ ካርሎ ዩነቨርሲቲ የተደረገ ጥናት በሳኦ ፖሎ 33 በመቶ የሚሆኑት የፓርቲ አባላት ሴቶች መሆናቸውን አሳይቷል።

ስለዚህ በቻይና ሴቶች የሚገባቸውን ቦታ ባያገኙም ችግሩ ግን የእርሷ ብቻ አይደለም።