"የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን እናጠፋለን ብለን አልሸባብን ፈጠርን"

በሞቃዲሾ በቅርቡ የደረሰው ፍንዳታ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በሞቃዲሾ በቅርቡ የደረሰው ፍንዳታ

በሶማሊያ አሰቃቂ የሚባለውን የቦምብ ፍንዳታ፤ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ለሶማሊያ የሚሰጠው ድጋፍ መቀነሱ እንደ አንድ ምክንያትነት ያነሱት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ-ማርያም ደሳለኝ ናቸው።

ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከፓርላማው የተነሱ ጥያቄዎችን በመለሱበት ወቅት ነው የተናገሩት። የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሊያ የነበረው ጣልቃ ገብነት ቢተችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልሻባብን በመዋጋትና መንግስት አልባ በነበረቸው ሶማሊያም መንግስት እንዲመሰረት ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተችም ተናግረዋል።

"ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ለሶማሊያ የሚሰጠውን ድጋፍ ነፍጎናል፤ ሰላምንና እርጋታን ለመፍጠር የተሰማራውን የአፍሪካ ህብረት ሰላማዊ አስከባሪ ኃይል ሰራዊት ቁጥሩ እንዲቀንስ ቢደረግም እኛ በራሳችን በጀት እየሰራን ነበር አሁንም አጠናክረን እንቀጥላለን። "ብለዋል።

የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት የፈረሰው አማፂያን የሲያድ ባሬን መንግሥት ሠራዊት አሸንፈው የበላይ ሆኖ ሃያል ሆኖ የወጣ ኃይል በጠፋበት ጊዜ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሃገሪቱ መንግሥት ኣልባም ሆና ከ20 ዓመታት በላይ ዘልቃለች።

በሶማሊያ መንግሥት ለመመስረት በተለያዩ ሃገራት አደራዳሪነት በርካታ የሰላም ሂደት ሙከራዎች ተደረገው ነበር። የተባበሩት መንግሥታት፣ አውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረት ከሰላም ሂደቶቹ ጀርባ ነበሩ።

የዕርቅ ሂደቶቹ የተለያየ መልክ የነበራቸው ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ የአደራዳሪዎቹን ሃገራት ብሔራዊ ጥቅም መሰረት ያደረጉ እንደነበሩ የፖሊቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ የተደረገው ተደጋጋሚ የሰላም ሂደት በንፅፅር የተሳካ እነደነበር ይነገራል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና ያለው ፌደራላዊ የሽግግር መንግስት ለማቋቋምም ተችሏል።

ባለፈው ዓመት በምርጫ ለመጣው መደበኛ መንግሥትም መሰረት ሆኗል። አሁንም ሶማሊያ የጦር ቀጠና እንደሆነች ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መረጋጋትን እየፈጠርን ነው በሚሏት ሶማሊያ የሃገሪቱን የደህንንት ችግር በዘላቂነት ከመፍታት አንፃር ግን የኢትዮጵያ ሚና እንዴት ይታያል?

ታሪካዊ ቁርሾ

ኢትዮጵያ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን ለመቆጣጠር ብቸኛው አማራጭ ሠራዊቷን ወደ ሶማሊያ ማስገባት ነበር ወይ? ለሚለው ጥያቄ የአፍሪካ ቀንድ የታሪክ፣ የግጭቶችና የደህንነት ተንታኝ የሆኑት ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ሲመልሱ በቀጥታ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መፈፀም አደገኛነቱን ያስረዳሉ።

በተለይም ኢትዮጵያና ሶማሊያ ካላቸው የታሪክ ቁርሾ አንፃር የኢትዮጵያ ሠራዊት ሶማሊያ ውስጥ ገብቶ በቋሚነት መንቀሳቀሱ ለእስላማዊ አክራሪ ቡድኖች ከፍተኛ መነቃቃትን እንዲሁም ትልቅ ካርድ የመዘዙበት ጉዳይ ነው።

"የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን እንደ ሃገር እናጠፋለን ብለን ገብተን አልሻባብን ነው የፈጠርነው" የሚሉት ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ፤ ታሪኩ ተቀይሮ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር፤ ክርስትና ከእስልምና ጋር የሚያደርጉት ጦርነት ተደርጎ መልኩ ተቀይሯል ይላሉ ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የኢትዮጵያ ሰራዊት በሶማሊያ

በተለያዩ ጊዜያት ሶማሊያን እንደ መነሻ አድርገው አካባቢውን ለማተራመስ የሞከሩ እስላማዊ ቡድኖች እንደነበሩ የሚናገሩት ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ አል ኢትሃድ አል ኢስላሚያ የተባለውን ቡድን ያስታውሳሉ።

"የእስልምና ፍርድ ቤቶች ኅብረት ወይም አልሸባብ ከመምጣታቸው በፊት ሶማሊያ ውስጥ የፀጥታ ስጋት በነበረባት ወቅት ኢትዮጵያ ሠራዊቷን ማስገባቷ አዲስ ነገር አይደለም" ይላሉ ፕሮፌሰር መድሃኔ።

ከዚያም ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሶማሊያን በተመለከተ፤ የተረጋጋች ሶማሊያ መኖሯ ለኢትዮጵያ ደህንነት እንደሚጠቅም ቢታመንም የአክራሪ እስላማዊ መንግሥት ወይም ቡድን ቁጥጥር እንዲኖር ግን አትሻም።

በተቃራኒው የሶማሊያ ፖለቲካ ተንታኞች "ኢትዮጵያም ትሁን ኬንያ የተረጋጋች ሶማሊያን ማየት አይፈልጉም" ቢሉም ፕሮፌሰር መድሃኔ፤ ይህን ካለው ታሪካዊ ቁርሾ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ።

"ይሄ አስተሳሰብ በሶማሌ ብሄርተኞች በኩል በከፍተኛ ሁኔታ ነው የሚንፀባረቀው፤ እያደገ ከመጣው የደህንነት ትንተና ጋር በፍፁም አይገናኝም" ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት በቀድሞ ጊዜ ድንበርን ብቻ ማስጠበቅ የነበረው ተቀይሮ በሃገሮች መካከል የህዝብና የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ በመኖሩ ሁኔታውን ሊለውጠው ችሏል።

ከዚህም በተጨማሪ አካባቢው በቀላሉ ለግጭት ተጋላጭ በመሆኑ ነገሩ በቸልታ እንደማይታይም ይናገራሉ።

ፕሮፌሰር መድሃኔ "የተዳከመች ሶማሊያ ለኢትዮጵያ ትጠቅማለች የሚል አስተሳሰብ የለም፤ ይህ ጊዜ ያለፈበት አመለካከት ነው" ይላሉ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የአፍሪካ ህብረት ሰላማዊ አስከባሪ ኃይል ሰራዊት በሶማሊያ

አቅመ ቢሱ የሽግግር መንግ

የሽግግር መንግሥቱ በዓለም ዓቀፍ ዕውቅና ከማግኘቱ ውጪ ራሱንና መላውን የሶማልያ ግዛት ለመከላከል የሚያስችል የፖለቲካ ብቃትም ወታደራዊ አቅምም አልነበረውም።

በመሆኑም በዳሂር አዌይስ የሚመራው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት የሃገሪቱ ደቡባዊ ክፍልን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር በኢትዮጵያም ላይ ጅሃድን ማወጁ ይታወሳል።

ኅብረቱ "ታላቋ ሶማሊያ" የሚለውን የቆየ አስተሳሰብ ማቀንቀን ጀምሮ የነበረ ሲሆን፤ በተለይ በኢትዮጵያ የሚገኘውን አዋሳኝ የኦጋዴን አካባቢን ለማስመለስም ዝቶ ነበር።

በዚህም ምክንያት፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ በወቅቱ ከሽግግር መንግሥት በቀረበው ግብዣ መሰረት፤ ወደ ሶማልያ ጣልቃ ለመግባት በፓርላማ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በኩል ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ በሶማሊያ ላይ ብዙ ጥናቶችን ያደረገችው ቅድስት ሙሉጌታ "ዘ ሮል ኦፍ ሪጂናል ፓወርስ ኢን ዘ ፊልድ ኦፍ ፒስ ኤንድ ሴኩሪቲ ዘ ኬዝ ኦፍ ኢትዮጵያ" በሚለው ፅሁፏ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግሮች፣በአገሪቷ ውስጥ ፖለቲካዊ መስማማቶች ቢጎሉዋትም ከድንበሯ አልፋ \

በሌሎች አገራት በምታደርገው ተፅእኖ የኃያል አገርነትን ሚና ትጫወታለች።

ኢትዮጵያ ያላት ጠንካራ የሰራዊት ሃይል፣ከፍተኛ የህዝብ ቁጥሯ፣ በአንፃራዊነት ያላት የአገሪቱ መረጋጋትና የዲፕሎማሲያዊ ጥንካሬ አገሪቷ በክልሉ ላይ የምትጫወተውን ሚናና ቦታ እንዲሁም የክልሉን ሰላምና የደህንነት ጅማሮዎችን እንድትመራ አስችሏታል በማለት ፅሁፉ ያትታል።

ከእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት በኩል "ግልፅና ወቅታዊ ስጋት" ተደቅኖብናል በማለት ለማሳመን ቢሞክሩም፤ በተለይ በወቅቱ የምክር ቤቱ አባል የነበሩት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ጣልቃ ገብነቱ በኢትዮጵያ ላይ 'ዘላቂ ጥላቻን' ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀው ነበር።

ከኅብረቱ ጀርባም በርካታ ሃብታም የአረብ ሃገራት እንደነበሩ በመተንተን፤ ኢትዮጵያ የማትወጣው ጦርነት ውስጥ እየገባች እንደነበርም የተለያዩ ስጋቶች ሲቀርቡ ነበር።

አሜሪካም ከጣልቃ ገብነቱ ጀርባ እንደነበረች ቢነገርም፤ በወቅቱ ሾልኮ የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው አሜሪካ ስጋቷን ለኢትዮጵያ መንግሥት ገልፃ ነበር።

በተለይ አፍሪካ የሚገኘው የአሜሪካ ጦር (አፍሪኮም) የሚመሩት ጀነራል ጆን አቢዛይድ "የቸኮለ ውሳኔ" በማለት የጣልቃ-ገብነቱን አላስፈላጊነት ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ መምከራቸው ይነገራል።

በተቃራኒው የኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነት የአሜሪካ ፖሊሲ ቅጥያ ተደርጎ እንደታየ የሚያስረዳው የቅድስት ፅሁፍ የአሜሪካ መንግስት ራሱ በኢትዮጵያ ደህንነት መረጃዎች ጥገኛ እንደሆነም ይጠቁማል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውጭም ውስጥም ከባድ ተቃውሞ ይግጠማቸው እንጂ በድምፅ ብልጫ ሃሳባቸውን በምክር ቤቱ አስፀድቀው ወታደራዊ ኃይል ወደ ሶማሊያ መላክ ችለዋል።

ከኅብረቱ ጀርባ ከኢትዮጵያ ግብፅንና ኳታርን ጨምሮ በርካታ ሃገሮች እንደበሩበት ሲታሙ፤ የኤርትራ መንግሥትም ኢትዮጵያን ለማጥቃት ከህብረቱ ጀርባ አለ የሚል ክስም ቀርቦ ነበር።

ኤርትራ ብታስተባብልም የተባበሩት መንግሥታት ኮሚቴ ባደረገው ማጣራት የኤርትራ መንግሥትን ጣልቃ ገብነትን ማረጋገጥ መቻሉን ባቀረበው ሪፖርት መግለፁ ይታወሳል።

ወታደራዊው ዘመቻና መዘዙ

በ2001 ዓ.ም የሁለት ዓመት ቆይታውን አጠናቆ ወደ ሃገሩ የተመለሰው የኢትዮጵያ ሠራዊት፤ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረትን በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ማፈራረስ ችሎ ነበር። ነገር ግን የኅብረቱ የወጣቶች ክንፍ እንደሆነ የሚነገርለት አልሸባብ በመባል የሚታወቀው አክራሪ ቡድን ማንሰራራቱ ይታወቃል።

ኢትዮጵያም ለሁለተኛ ጊዜ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ አዝምታ አልሸባብን መውጋት ከጀመረች በኋላ ሌሎች ሃገራትም በአፍሪካ ኅብረት በኩል ወደ ሶማሊያ ገብተዋል።

አልሸባብ ከቀደመው እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅበረት ቡድን የባሰ ፅንፈኛ እንደሆነ ይነገርለታል። ፕሮፌሰር መድሃኔም የቡድኑ አፈጣጠር በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነት ጋር ያገናኙታል።

ዛሬ ከሃገሪቱ ጠፍቷል ሲባል፤ ነገ በዋና ከተማዋ ሶማልያ ከባድ ጥቃት ሲፈፅም ይስተዋላል። ጨርሶ ማጥፋት ይቅርና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቶ በቅርቡ በሞቃዲሾ የተፈፀመውን ዓይነት የሽብር ድርጊት በጎረቤት ሃገራት ጭምር ለመፈፀም በቅቷል።

ሶማሊያውያን ከሁሉም አቅጣጫ በሚካሄዱ ዘመቻዎች እና በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ከባዱን ዋጋ ሲከፍሉ ኖረዋል።

የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት በሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ መፈናቀሉን እንዲሁም የኢትዮጵያ ሠራዊትን ከሽግግሩ መንግስት ጋር በመተባበር በተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይከሳል።

የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መዘዙ ሰፊ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር መድሃኔ "ሶማሊያዊያን እራሳቸው የማያደርጉትን በጎረቤት አገር በተለይም ደግሞ ታሪካዊ ቁርሾ ባለበት ሁኔታ የሚደረግ ሃገር የመገንባትና የሰላም ግንባታ ጥረት ብዙ ኪሳራዎች አሉት" ይላሉ።

የቅድስት ፅሁፍ እንደሚያትተውም ኢትዮጵያ ራሴን ለመከላከል ነው ብትልም እንደ "ወራሪ" ነው የታየችው፤ ጣልቃ መግባቷ ስህተት እንደነበረና ከዚህ በፊት አልኢትሀድ ላይ እንዳደረገችው የእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረት የያዛችውን ቦታዎች ለይታ መምታት ሰራዊቱንም ማዳከም ትችል ነበር።

የተለያዩ የሶማሊያ የፖለቲካ ተንታኞችም የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ እንዲሁም ሌሎች ሃገራት በየዓመቱ ለአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል የሚያደርጉትን በቢሊየኖች ዶላር የሚቆጠር መዋዕለ-ንዋይ ድጋፍ የሶማሊያን ሰራዊት ለመገንባት ቢፈስ ለውጥ ይመጣል ይላሉ።

''የጦር ሠራዊቱን ለማሰልጠን የተለያዩ ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም መፍትሄ አላመጡም ባጠቃላይ ችግሩ ጣልቃ ከመግባቱ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው።" ይላሉ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የሶማሊያ ምርጫ

"ሁሉም በውጭ ጣልቃ ገብነት የመጡ የሰላምም ይሁኑ የመንግሥት አወቃቀር አማራጮች የሶማሊያን ባህላዊና ታሪካዊ እውነታዎችን ያገናዘቡ አይደሉም" የሚሉት ፕሮፌሰር መድሃኔ፤ በተጨማሪም "እነዚህ መንግሥታትም ይሁኑ ተቋማት እነሱ የሚያዉቁትን ምዕራባዊ የመንግሥት አወቃቀር በፍጥነት ለመጫን ተሞክሯል" ይላሉ።

በሶማሊያውያን ተነሳሽነት ቀስ በቀስ እያደገ ሳይሆን በአቋራጭ ማዕከላዊ መንግሥት ለመመስረት ቢሞከርም መድሃኔ እንደሚሉት የትኛውም የሶማሊያ የፖለቲካ ቡድንም ሆነ ሃይል ማዕከላዊ መንግሥት ለመመስረት አቅም እንደሚያጥረው ያስረዳሉ።

እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጡትም በየአካባቢው የተፈጠሩ የሰላም ዞኖችና አካባቢዎችን በማጠናከር ዘላቂ የፌደራል መንግሥትን ማምጣት አለመቻሉን እንደ እክል ያዩታል።

ሶማሊያ አለመረጋጋት እንዲቀጥል የሚፈልግ ላት ይኖሩ ይሆን?

ሶማሊያን ተረጋግታ እንደሃገር እንድትቆም ብዙ መንግሥታዊ፣ አህጉራዊና ሌሎች ተቋማት በቢሊዮን የሚቆጠር መዋዕለ-ነዋይ እያፈሰሱበት ቢሆንም ችግሩ ሊፈታ አልቻለም።

"በሶማሊያ ግጭት የተነሳ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ፍላጎቶች ተፈጥረዋል። የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶችም በግጭቱ ተጠቅመዋል። በዚህም የተነሳ የተለያዩ ኃይሎች ግጭቱና ጦርነቱ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ"ፕሮፌሰር መድሃኔ ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሠራዊት በሃገሪቷ ባሉ አለመረጋጋቶችም ይሁን በተለያዩ ምክንያቶች ከሶማሊያ ወጥቶ ኢትዮጵያ ያላት ሚና ቢቀንስም የኬንያ፣ ኡጋንዳና ቱርክ የመሳሰሉት ሃገራት ሚና በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በሶማሊያ ላይ ያላት ሚና እንደ ሃገር ከፍተኛ ባይሆንም፤ ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ወታደራዊ ዘመቻዎች ሳቢያ ሶማሊያውያን ለኢትዮጵያ አሉታዊ ዕይታ እንዲኖራቸው አድርጓል።

ለዚህም ማሳያ በቅርቡ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት ተፎካካሪዎች ለቅስቀሳቸው ፀረ-ኢትዮጵያ እንዲሁም ጣልቃ የገቡ ኃይሎችን ማዕከል አድርገው ነበር።

ፕሮፌሰር መድሃኔም እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጡት ሶማሊያውያን በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ እራሳቸው ባህል በመመልከት በድርድር ባህላቸው፤ ከማዕከላዊ መንግሥት ወደታች ያተኮረ ሳይሆን ከታች ወደ ማዕከላዊ መንግሥት የሚመጣ ማዋቀር መገንባት ያስፈልጋቸዋል ይላሉ።