ካለሁበት 6፡ ''ከሀገር ቤት የስደት ኑሮዬ ይሻለኛል''

ፋና ተክላይ Image copyright ፋና ተክላይ

ፋና ተክላይ እባላለሁ፤ በሊባኖስ ቤይሩት መኖር ከጀመርኩኝ ሁለት ዓመት ሆኖኛል፤ እንዴት ወደ ስደት እንደመጣሁኝ ላጫውታችሁ ነው ።

በትግራይ በሰሜናዊ ምዕራብ ዞን፡ በታሕታይ ቆራሮ ወረዳ፡ ሰቀላ-ቆየጻ በሚባለ አካባቢ ነው የተወለድኩት።

እሰከ ዘጠነኛ ክፍል ድረስ ከቤቴ ለሁለት ሰዓታት በእግር እየተመላለስኩኝ ተማርኩኝ።

11 ዓመት ሲሞላኝ ግን ወላጆቼ በእድሜ በጣም ከሚበልጠኝ ሰው ጋር ዳሩኝ።

ከጥቂት ጊዜ በኃላ ግን ባለቤቴ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ውትድርና ዘመተ።

እኔም ትምህርቴን ብቀጥልም ቤተሰቦቼ ግን ትምህርት ቤት ሳይሆን የትም ስዞር የምውል ስለሚመስላቸው እንድማር አልፈቀዱልኝም።

በዚህም የተነሳ በሁለታችን ቤተሰቦች መካከል አለመግባባት ስለተፈጠረ እኔ መቋቋም አልቻልኩም።

በመጨረሻም በ1994 ወደ መቐለ ጠፍቼ ዘመዶቼ ጋር ባርፍም እዚህም ማረፍ አልቻልኩም ፤ ነጋ ጠባ ትዳርሽን ትተሽ መጣሽ እያሉ ያሳቅቁኝ ነበር። ግን አማራጭ ስላልነበረኝ ሁሉንም ችዬ እኖር ነበር።

ከ3 ዓመት በኋላ ግን ፍሬአብዮት በሚባል ትምህርት ቤት ያቋረጥኩትን የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቴን ጀመርኩኝ።

በዚህ ጊዜ ሞራሌ በተሰበረበት፤ አይዞሽ የሚል ሰው ባጣሁበት ጊዜ ከሌላ ወንድ ጋር ተዋወቅኩኝና ትዳር መሰረትኩ።

በጣም ያስብልኝ፣ እንድማርም ያበረታታኝ ነበር። እኔም ከ10ኛ ክፍል በኋላ የኮሌጅ ትምህርት ጀመርኩኝ።

ሆኖም ባለቤቴ በስራ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ሲቀይር እኔም ተከትየው ሄድኩኝ ።

በመሀከላችን ግን አለመግባባት ተፈጠረ ፤ልጅ መውለድ በጣም ብፈልግም ሊፈቅድልኝ አልቻለም።

ያኔ በውጪ የሚኖሩ ብዙ ጓደኞቼ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለተሻለ ህይወት እንድቀላቀላቸው ጫና ያሳድሩብኝ ነበር።

በኋላ ቪዛ ሲልኩልኝ በ2001 ዓ.ም ወደ ኩዌት ተሰደድኩ።

ኩዌት መጀመሪያ ላይ እንደጠበቅኳት ኣላገኝኋትም፤ ምክንያቱም በሌሎች ሰዎች አማካኝነት ድጋፍ ካልተገኘ በተሻለ የስራ ቦታ መስራት አይቻልም።

እኔም በሰው ቤት በቤት ሰራተኝነት ተቀጥሬ መስራት ጀመርኩኝ።

እዚህ እንድመጣ ያበረታቱኝ ጓደኞቼ እንኳን አልተቀበሉኝም።

ለኔ ደግሞ የመጀመርያ የስደት ኑሮዬ ስለነበረ ከቤተሰብ ተለይቶ መኖር በጣም ከበደኝ።

አሰሪዎቼን አላውቃቸውም፤ በዛ ላይ በማይገባኝ ቋንቋ ሲጯጯሁ የሚበሉኝ ይመስለኝ ነበር። ሁሉም ነገር ጨለመብኝ።

በመምጣቴ ብጸጸትም ወደ ኃላ መመለስ ስለማልችል ለሰባት ወራት በለቅሶ አሳለፍኩኝ።

Image copyright ፋና ተክላይ

"የኔ ህይወት ውስብስብ ነው"

ኩዌት በሄድኩበት ግዜ፤ ባለቤቴ የፈለገ ቦታ ቢሆንም ሳይደውልልኝ አይውልም ነበር።

ከሶስት ዓመታት በኋላ በኩዌት የነበረኝን የስደት ቆይታ ጨርሸ፤ ወደ ሀገር ቤት ስመለስም ባለቤቴን ለማግኘት ትልቅ ጉጉት ነበረኝ።

እርሱም ደስ ብሎት ከአየር መንገድ ተቀብሎ ወደ ቤት ወሰደኝ፤ ቤቴ ግን እንደተውኩት አልጠበቀኝም።

ወደ ቤት ስገባ አንዲት ሴት አግኝቼ ሰራተኛው እንደሆነች ነገረኝ።

አመሻሽ ላይ ግን በመካከላቸው ጭቅጭቅ ተፈጠረ። ለካ ሁለተኛ ሚስት አስቀምጦልኝ ኖሯል።

ከዛ በኋላ መስራት እንዳለብኝ ወሰንኩና እና የፀጉር ስራ ትምህርት ተምሬ፣ የሚያስፈልጉ እቃዎቼንም ገዝቼ ለመስራት ብሞክርም መረጋጋት አልቻልኩም።

ውስጤ ሰላም አጣ፤ ሰዎችም ከአሁን በፊት የነበረኝን ህይወት በማነፃፀር ከንፈር ይመጡልኝ ጀመር።

ይህንኑ መቋቋም ቢያቅተኝ፤ በድጋሚ ፊቴን ወደስደት አዞርኩና ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጓዝኩኝ።

ለሁለት ዓመታት በቤት ሰራተኝነት እና ፀጉር ቤት በፈረቃ እሰራ ነበር።

ሀገር ቤት እያለው የደረሰብኝ በደልና ከማህበረሰቡ ይደርስብኝ የነበረው ስነልቦናዊ ስብራት የስደት ኑሮየ አሜን ብየ እንድቀበለው አድርጎኛል።

እናም አሁንም ለተሻለ ኑሮ ለሶስተኛ ጊዜ እግሮቼ ወደሌላ ስደት ወደ ሊባኖስ መሩኝ።

በሊባኖስም የምሰራው የሰው ቤት ተቀጥሬ ቢሆንም የተሻለ የስራ ሰዓትና ክፍያ አለኝ።

በሕይወቴ ሶስት የአረብ አገራት፤ሶስት ስደት አይቻለሁ።

መጀመሪያ ላይ እንደመጣሁ ምግባቸው በጣም ያስጠላኝ ነበር። ሌሎቹን ቀሰ በቀስ መላመድ ብችልም አባጨጓሬ የሚመስል " ሽሪምፕ" የሚባል ከባህር የሚወጣ ምግባቸውን ግን አሁንም እንደጠላሁት ነው።

Image copyright ፋና

" እኛን አማክራችሁ ነበር እንዴ የመጣችሁት ?"

በቤይሩት ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ፤ብዙ ችግርም ያጋጥማቸዋል። ታመውና አብደው በየጎዳናው ሲሄዱ አያለሁ።

አንዳንዶቹ በደላላ መጥተው በአሰሪዎቻቸው ይበደላሉ። ይህንን አይተን በሊባኖስ ወደሚገኘው ኢትዮጵያ ኤምባሲ ስንደውል የሚሰማን የለም።

እህቶቻችን ችግር አጋጠማቸው ስንላቸው "ለኛ አማክራችሁ ነበር እንዴ የመጣችሁት?" ይሉናል።

የሌሎች ሀገራት ዜጎች ኤምባሲዎቻቸው ስለሚተባበሯቸው ጥሩ ክፍያ እና እረፍት ያገኛሉ። ለኛ ግን እንደ ዜጋ የሚተባበረን የለም።

እርሰ በርሳችን ግን እንተሳሰባለንን። በበዓላት የምንገናኛባቸው አጋጣሚዎች አሉ። እዚህ ካለው ስደተኛ ጋር መልካም ጊዜ የምናሳልፍባቸው የኢትዮጵያ ሬስቶራንቶችም አሉ።

'' ከሀገር ቤት የስደት ኖሮዬ ይሻለኛል''

ወደሀገሬ ብገባ የሰዎች አሽሙር ብሰደድ የስደተኛ በደል ነው የሚጠብቀኝ። ሁሉም በደል ነው። ባወዳድር ግን ተሰድጄ የምኖረው ኑሮ ይሻላል።

እኔ አብዛኛውን ጊዜ ትርፍ መፅሃፍ በማንበብ ነው የማሳልፈው፣ ቤተክርስትያንም እሄዳለሁ። የአሰሪዎቼ ቤተሰቦችም ትንሽ ስለሆኑ ነፃነት ይሰጡኛል።

ጥዋት ከመኝታ ቤቴ ተነስቼ የበረንዳ መሰኮት ስከፍት፡ ከፊት ለፊቴ የሚታየኝ ባህር አለ። ራሴ የምንከባከባቸው አትክልትም አሉኝ።

ይህ ለመንፈሴ እርካታ ይፈጥርብኛል። ትናንት ያሳለፍኩት ሕይወት ጠንካራ አድርጎኛል። ስለነገ ሳልጨነቅ ደስተኛ ሁኜ ለመኖር እጥራለሁ።

የተለያዩ ጉዳዮችን በፌስቡክ አጋራለሁ። በፌስቡክ ያገኝኋቸው ጥሩ ጓደኞች አሉኝ።

በተቻለኝ ሁሉ ከማገኘው ደሞዝ መፅሃፍትን በመግዛት ለትምህርት ቤቶች መለገስ ያስደስተኛል።

Image copyright ፋና ተክላይ

ባለፈው ዓመት በትግርኛ ቋንቀ የተፃፉ 350 መጻህፍትን ለትምህርት ቤቶች ለግሻለሁ።

የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ በሌሎች የትምህርት አይነቶች ጎበዝ ብሆንም፤ በአማርኛ ግን ሰነፍ ስለነበርኩ በዚህ የተበሳጨ አንድ ዘመዴ ዶሮ ሽጦ መፅሃፍ ገዛልኝ።

ያቺ የመፅሃፍ ስጦታ ለሱ ትንሽ ብትሆንም ለኔ ግን በሀይወቴ የማልረሳት እና ለሌሎች ሰዎች መፅሃፍ እንዳበረክት ምክንያት የሆነችኝ ስጦታ ናት።

በስደት ሕይወቴ አጋጠመኝ የምለው ከባድ ነገር ቢኖር ሳዑዲ አረቢያ በነበርኩበት ጊዜ በጣም ታመምኩኝ።

ወደ ሊባኖስ እንደመጣሁ ደግሞ ሶሪያ እና እስራኤልን በሚያዋስን ድንበር አካባቢ ስሰራ አካባቢው በጣም የሚያስፈራ ሁልጊዜም ወታደሮች የሚታዩበት ነበር።

ያኔ አሰሪዎቼ ለሶስት ወራት ቤታቸውን ትተው ወደ ሌላ አገር ሲጓዙ በማላውቀው ሀገር ለብቻዬ መኖር በጣም እንደከበደኝ አስታውሳለሁ

ተመልሰው ከመጡ በኋላም በተመሳሳይ ወደ ሌላ ሀገር ለመሄድ ሲዘጋጁ ዳግመኛ ለብቻየ በተዘጋ ቤት መቆየት አልፈለግኩም። እናም አንድ ነገር ማድረግ እንደለብኝ ወሰንኩኝ።

ከዛ ቤት ጠፍቼ ለሶስት ሰዓታት ያክል በማላውቀው መንገድ በሌሊት የእግር ጉዞ ጀመርኩኝ።

በሌሊት በዛ ላይ የዝናብ ዶፍ እየወረደብኝ ወደ ከተማ ገባሁኝ። ይህ አጋጣሚ በስደት ሕይወቴ የማልረሳው ከባድ አጋጣሚ ነው።

ድንገት አሁን ካለሁበት ራሴን ወደ ሌላ አካባቢ መላክ ብችል ራሴን በትግራይ ክልል በሽረ እንዳስላሴ ከዛም በመቐለ ከተማ አገኛት ነበር።

ለላይን ጽጋብ እንደነገረቻት

ካለሁበት 7፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ካምቦዲያ መኖር እፈልግ ነበር

ካለሁበት 8፡ ኢትዮጵያዊው የበረዶ ሸርተቴ ተወዳዳሪውና አስተማሪው በጃፓን

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ