ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች በኬንያ ምርጫ አለመረጋጋት ሊከሰት ይችላል ሲሉ እሰጠነቀቁ

የተቃዋሚዎች ስብሰባ Image copyright AFP

ቀጣይ ሃሙስ ሊካሄድ በታቀደውና ዋነው ተቃዋሚ ፓርቲ አልሳተፍበትም ባለው የኬንያ ዳግም ምርጫ 'እየጨመረ በመጣ የደህንንት ስጋት ውስጥ ነው' ሲሉ የምዕራባውያን ሃገራት ልዑካን አስጠነቀቁ።

በምርጫ ሃላፊዎች ላይ ያነጣጠረ የዛቻ ንግግርና ጥቃት በሃገሪቷ ውስጥ ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ እንቅፋት እየሆነ ነው ሲሉ የ20 ሃገራት ተወካዮች ስጋታቸውን ገልፀዋል።

የኬንያ አቃቢ ህግ የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ራይላ ኦዲንጋ እህት የሆነችውን ግለሰብ 'ግጭትን በመቀስቀስ' እከሳለሁ ብሏል።

ራይላ ኦዲንጋ ሃሙስ ሊካሄድ የታቀደውን ምርጫ እንዳይካሄድ ሰልፍ በመጥራት አስቆማለሁ ብለዋል።

ራይላ ቁልፍ የሆኑ የምርጫ ማሻሻያዎች ሳይካሄዱ ምርጫ አይኖርም ብለዋል። ይህም ማሻሻያ የምርጫ ኮሚሽኑን ሃላፊ ከስልጣን ማስነሳትን ያጠቃልላል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ 2 ተካሂዶ በነበረው ምርጫ ኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያት አሸናፊ መሆነቸውን ካወጀ በኋላ በተነሱ ግጭቶች እስካሁን ከ70 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የምርጫ ውጤቱ የተዛባ ነገር ተስተውሎበታል በሚል ሰርዞ ዳግም ምርጫ እንዲካሄድ ማዘዙ ይታወሳል።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ አሁን ድረስ ምንም የተቀየረ ነገር የለም ይላሉ።

የውጪ ሃገራት ልዑካን በምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር ውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ አሳስቦናል ብለዋል።

የአሜሪካ አምባሳደር ቦብ ጎዴግ የ20 ሃገራትን ልዑካን ወክለው ባደረጉት ንግግር 'ከመገንባት ይልቅ ማፍረስ ይቀላል። ይህም አደገኛ ነው። መቆም አለበት' ሲሉ አሳስበዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት የምርጫ ኮሚሽኑ ከፍተኛ ሃላፊ ከደረሳቸው ተደጋጋሚ የግድያ ማስፈራሪያ በኋላ ወደ አሜሪካ ሸሽተው ሄደዋል።

ሮስሊ አኮምቤ እንዳሉት ኮሚሽኑ 'በፖለቲካ ተፅእኖ ስር ነው ያለው' መግባባት ላይ መድረስም ሆነ ምንም አይነት እርምጃ መውሰድ አይቻልም ብለዋል።