የቺቦክ ማስታወሻ ደብተሮች፡ የቦኮ ሃራም እገታ የጽሑፍ ቅጂዎች

ናዖሚ "ለማስታወሻ ነው የጻፍኩት"

ባለፈው ግንቦት ከቦኮ ሃራም እገታ ከተለቀቁት ልጃገረዶች መካከል አንደኛዋ ለጋዜጠኛ አዳዎቢ ትሪሻ ንዋኡባኒ ለሶስት ዓመታት በታሰረችበት ወቅት ስላስቀመጠችው የማስታወሻ ደብተር አጫውታታለች።

የ24 ዓመቷ ናዖሚ አዳሙ አብረዋት ይማሩ ከነበሩት መካከል በእድሜ ትልቋ ነበረች።

እ.አ.አ በ2014 እርሷን ጨምሮ በአብዛኛው ክርስቲያን የነበሩ ከ200 በላይ ሴት ተማሪዎች ታግተው በሰሜን ናይጄሪያ ወደሚገኘው ሳምቢሳ የተሰኘ የቦኮ ሃራም መደበቂያ ደን ተወሰዱ።

በእስር በነበሩበት ጊዜ ሴቶቹ ቁርዓን እንዲቀሩ ይደረግ ስለነበር ማስታወሻ የሚይዙበት ደብተር ተሰጥቷቸው ነበር።

ከመካከላቸው ግን አንዳንዶቹ ሴቶች የእገታውን ማስታወሻ ለመያዝ ተጠቀሙባቸው። ታጣቂዎቹ ባገኟቸውም ጊዜ ደብተሮቹን አቃጠሉባቸው።

ናዖሚ ግን የራሷን መደበቅ ችላለች። አሁን 20 የሞላት የቅርብ ጓደኛዋ ሳራ ሳሙኤልና ሶስት ሌሎች ልጃገረዶችም እንዚህን ደብተሮች ገጠመኞቻቸውን ለመመዝገብ ተጠቀሙባቸው።

አጭር የምስል መግለጫ ለማስታወሻ የተጠቀሙበት 2 ባለ 40 ገጽ ደብተሮች ተርፈዋል

የተገኙትም ማስታወሻዎች በመለስተኛ እንግሊዘኛና በደካማ ሃውሳ የተጻፉ ሲሆኑ ያለ ቀናት የተመዘገቡ ቢሆንም በታገቱባቸው የመጀመሪያ ወራት አካባቢ የተጻፉ መሆናቸው ግልጽ ነው።

ከመዘገቧቸው ብዙ ትውስታዎች መካከል አሥሩን መርጠን በሚቀጥሉት 10 ቀናት ይዘንላችሁ እንመጣለን።

1) ለማገት አላሰቡም ነበር

በአውሮፓውያኑ ሚያዚያ 14, 2014 ዓ.ም የቺቦክ ትምህርት ቤት ላይ ጥቃት ያደረሱት ታጣቂዎች አመጣጣቸው ሞተር ለመስረቅ እንጂ ልጃገረዶቹን ለማገት አልነበረም ።

የፈለጉትም ሞተር የትኛው እንደነበር ግልጽ ባይሆንም የመኪና ይሁን ሌላ ለማወቅ አዳጋች ሆኗል።

ሆኖም በአካባቢው የግንባታ ሥራ እየተካሄደ ስለነበረ ድንገት ሲሚንቶ የሚያቦካውን ሞተር ፈልገው ሊሆን ይችላል፤ ይህም ሞተር ደረቅ መሣሪያዎችን ለመሥራት መጠቀም ስለሚቻል ሊሆን ይችላል።

ሞተሩን በአካባቢው ማግኘት ሲያቅታቸው ግን ሰብሰበዋቸው የነበሩትን ልጃገረዶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲነጋገሩ ግን መስማማት አልቻሉም ነበር።

"እርስ በርሳቸው መጣላት ጀመሩ። አንድ ትንሽ ልጅ ከመካከላቸው 'ማቃጠል አለብን' አላቸው። 'አይሆንም ወደ ሳምቢሳ መውሰድ አለብን' አለ ሁለተኛው። ሌላኛው ሰው ደግሞ 'አይ አይሆንም እንደሱ አናድርግ' አለና 'እንምራቸውና ከዚያ ወደ ቤተሰቦቻቸው ቤት እንሂድ' አለ። እየተከራከሩም ሳለ አንደኛው 'አይሆንም ባዶ መኪና ይዤ መጥቼ ባዶ መኪና ይዤ አልመለስም፣ ባይሆን ወደ [አቡባከር] ሼኮ [የቦኮ ሃራም መሪ] ይዘናቸው ከሄድን ምን ማድረግ እንዳለበን ያውቃሉ። "

አሰቃቂ የሆኑትን አማራጮች ካወጡ ካወረዱ በኃላ ሴቶቹን ይዘዋቸው ለመሄድ ወሰኑ ... ከዚያስ?