ራቃን ከምድረ ገፅ በማጥፋት ሩሲያ አሜሪካንን ወነጀለች

የፈራረሰችው ራቃ
አጭር የምስል መግለጫ የፈራረሰችው ራቃ

የሶሪያ አንዷ ከተማ የሆነችውን ራቃን አይኤስን ለመምታት በሚል የአሜሪካ ጥምረት ኃይል ከምድረ-ገፅ አጥፍቷል ሲል የሩሲያ መንግሥት ወንጅሏል።

የሶሪያ ዲሞክራቲክ ኃይል በአሜሪካ ከሚደገፈው የኩርድና የአረብ ዝርያ ካላቸው ወገኖች የተውጣጣ ቡድን ሲሆን ባለፈው ሳምንትም ራቃን በቁጥጥሩ ስር አውሏል።

ከአካባቢው የሚወጡ ምስሎች እንደሚያሳዩት ራቃ ፍርስርሷ መውጣቱን ሲሆን፤ የሩሲያ መንግሥት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተባበሩት ኃይሎች ህብረት ያወደማትን የጀርመን ከተማ ከድሬስደን ጋር ጉዳቱን አመሳስለውታል።

በአሜሪካ የሚመራው የጥምረት ኃይል በበኩሉ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየተሞከረ ነው ብሏል።

የሩሲያ መንግሥት ባለፈው ዓመት በአሌፖ ላይ የቦምብ ድብደባ ፈፅሞ ውድመት በማድረሱ የጦር ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ ሲከሰስ ነበር።

ከሦስት ወራት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጦር ወንጀል ላይ ያደረገው ምርመራዎች እንደሚያሳዩት ራቃ ውስጥ በሚያስደነግጥ ሁኔታ የሰላማዊ ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል።

የሶሪያ አቀንቃኞች የሟች ሰዎችን ቁጥር ከ1130 እስከ 1873 እንደደረሰ እየተናገሩ ሲሆን፤ እነዚህ ንፁሀን ዜጎች የሞቱት በአሜሪካ መራሹ ጦር ኃይልና በሶሪያ የዲሞክራቲክ ኃይል ጥቃት ምክንያት ነው ይላሉ።

የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም የራቃ ውድመት የድሬስደንን ጥፋት እንዳስታወሳቸው ተናግረዋል።

"በእንግሊዝና በአሜሪካ ጥምር ኃይል በሁለተኛው የአለም ጦርነት ከምድረ-ገፅ እንደጠፋችው ድሬስደን ራቃም ተመሳሳይ ዕጣ ደርሷታል" በማለት ማጅ ጌን ኢጎር ኮናሸንኮቭ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ምዕራባውያን የሰሩትን ወንጀል ለመሸፋፈን የገንዘብ ዕርዳታን ወደ ራቃ እየላኩ ነው ብለዋል።

በአሜሪካ የሚመራው ጥምር ኃይልና የሶሪያ የዲሞክራቲክ ኃይል ከአራት ወራት ፈታኝ ጦርነት በኋላ ለሦስት ዓመታት ሲመራት በአይ ኤስ ቡድን ቁጥጥር ስር የቆየችውን ራቃን አስለቅቀዋል።

በተጨማሪም የሶሪያን ትልቁና ከፍተኛ የገቢ ምንጭ የሚገኝበትን የአል ኦማር የነዳጅ ማውጫ ቦታንም በቁጥጥር ስር እንዳዋሉም ተናግረዋል።

የሶሪያ ዲሞክራቲክ ኃይል በበአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኘውን ዴይር አል ዙርን ለመቆጣጠር ትኩረት አድርጓል።

የሶሪያ መንግሥት የጦር ኃይል በሩሲያ አየር ኃይልና በኢራን የሚደገፍ ሲሆን አክራሪዎች ቡድኖችን እየተዋጋ ይገኛል።