የአይንስታይን ማስታወሻ በ1.6 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ

The two notes sold for $1.56m and $240,000 - way higher than their estimates Image copyright AFP

አንድ ሰው በሕይወቱ ደስተኛ ለመሆን እኒህን መመሪያዎች ተግባራዊ ቢያደርግ ብሎ አልበርት አይንስታይን በምክር መልክ ያሰፈረበት ማስታወሻ ሰሞኑን በ1.6 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ በእየሩሳሌም ከተማ ተሽጧል።

አይንስታይን ማስታወሻውን በአውሮፓውያኑ 1992 ለአንድ መልዕክተኛ በጉርሻ መልክ ነበር የሰጠው።

ወቅቱ አይንስታይን በፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት ያገኘበት ነበርና ለመልዕክተኛው ማን ያውቃል ወደፊት ጥሩ ዋጋ ያለው ዕቃ ይሆናል ብሎት ነበር።

በማስታወሻው አይንስታይን የረጅም ጊዜ ዕቅድን ማሳካት ማለት ደስታ መግዛት እንዳልሆነ ማስፈሩም ታውቋል።

ጀርመን የተወለደው ሳይንቲስት አይንስታይን በወቅቱ ወደ ጃፓን ለትምህርታዊ ጉዞ ሄዶ ነበር።

መልዕክተኛው አይንስታይን ወዳረፈበት ክፍል የተላከውን ለማድረስ ሲመጣ አይንስታይን ለጉርሻ የሚሆን አንዳች ገንዘብ አልነበረውም ነበር። በምትኩም ለመልዕክተኛው ማስታወሻውን ሰጠው።

Image copyright Getty Images

መመሪያው ባረፈበት ሆቴል ማስታወሻ ደብተር ላይ ያረፈ ሲሆን በአንድ ዓረፍተ-ነገር በጀርመንኛ ቋንቋ የተፃፈም ነበር።

"የተረጋጋ እና ትህትና የተመላበት ሕይወት ላቅ ያለ ደስታ ያመጣል። የስኬት ምንጭም ነው፤ እርጋታ የሰፈነበት ሕይወትም ይሆናል" ሲል ይነበባል ማስታወሻው።

ሌላኛውና በተመሳሳይ ወቅት አይንስታይን የፃፈው ማስታወሻ በ240 ሺህ ዶላር የተሸጠ ሲሆን "መልካም ፍቃድ ባለበት ሁሉ መንገድ አለ" የሚል ዓረፍተ-ነገር ያረፈበት ነው።

አጫራቾቹ ማስታወሻውን ለሽያጭ ካቀረቡበት ዋጋ እጅግ ልቆ እንደተሸጠ አሳውቀዋል።

ገዢው ማንነቱ እንዲታወቅ ያልፈለገ አንድ አውሮፓዊ ሲሆን፤ ሻጩም የመልዕክተኛው የቅርብ ዘመድ መሆኑም ታውቋል።

ተያያዥ ርዕሶች