ከእግር ኳስ ሜዳ ወደ ኮኛክ ጠመቃ

ለበርሚንግሃም ከ80 በላይ ጨዋታዎችን ተጫውቷል Image copyright JAMIE MCDONALD
አጭር የምስል መግለጫ ኦሊቪዬ ቴቢሊ ለበርሚንግሃም ከ80 በላይ ጨዋታዎችን ተጫውቷል

እንደሌሎች እግር ኳስ ተጫዋቾች ለስራ የሚነሳሳው ስታዲየም ውስጥ ደጋፊዎችን ሲመለከት አይደለም። እሱን የወይን ዘለላዎች የበለጠ ለስራው ያለውን ፍላጎት ከፍ ያደርጉለታል።

እግር ኳስ እና አልኮል አብረው የማይሄዱ ቢሆንም የቀድሞው የበርሚንግሃም ሲቲ ተከላካይ ኦሊቪዬ ቴቢሊ ግን ኮኛክ ማምረትን መርጧል።

የቀድሞው የሴልቲክና የበርሚንግሃም ተከላካይ አሁን በዓለማችን ታዋቂ በሆነው የፈረንሳይ የወይን እርሻ ውስጥ ኮኛክ ያመርታል። ኮኛክ ከሻምፓኝ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለው የአልኮል መጠጥ ነው።

የመጀመሪያውን የወይን እርሻ ገና ዕድሜው በአስራዎቹ መጨረሻ ላይ እያለ መግዛቱ ብዙዎች እንደሚያስቡት የቀድሞው እግር ኳስ ተጫዋች ቴቢሊ ገንዘቡን አነስተኛ ፕሮጀክት ላይ አለማፍሰሱን ያሳያል።

"የመጀመሪያ የፕሮፌሽናል ተጫዋችነት ውሌን ስፈርም ነው ሁለት ሄክታር መሬት የገዛሁት" ሲል በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ በሚገኘው ሳልስ ደ ኤንጅል በተባለች መንደር በሚገኘው እርሻ ውስጥ ሆኖ ነው ኦሊቪዬ ኃሳቡን ለቢቢሲ ያካፈለው።

" ለራሴ ጉዳት ቢያጋጥመኝና እግር ኳስን ባቆም ልሰራው የምችለው ነገር ሊኖረኝ ይገባል ስል እነግረው ነበር። ግዢውን የፈጸምኩት ፕሮፌሽናል ተጫዋች ከመሆኔ በፊት ለእረፍት ጊዜዬ የሚያስፈልገኝን የኪስ ገንዘብ የማገኘው እርሻዎቹ ላይ በመስራት ስለነበር ነው። ፕሮፌሽናል ተጫዋች መሆን ከባድ በመሆኑ ነበር ፊርማዬን እንዳኖርኩ እርሻውን ለመግዛት የወሰንኩት" ሲል ይገልጻል።

እ.አ.አ በ1993 ነበር ቴቢሊ በፈረንሳይ ሁለተኛ ሊግ ለሚጫወተው እና ቤተሰቦቹ ከአቢጃን መጥተው ከከተሙባት ከተማ ብዙም ለማይርቀው ኒዮር የፈረመው።

አጭር የምስል መግለጫ አዳዲስ የጠመቃ ዘዴዎችን እየተማረ ያለው ቴቢሊ

ይህ ጉዞ ወደ ሻቶሩ እና ሼፊልድ ዩናይትድ እንዲያመራ ዕድል ከፍቶለታል። እኤአ በ2000 በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፈ ሲሆን በ2001 ደግሞ በስኮትላንዱ ሴልቲክ በአንድ የውድድር ዓመት የሶስት ዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቅቷል።

ከበርሚንግሃም ጋርም ለአራት ዓመታት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለመጫወት ችሏል። ለካናዳው ቶሮንቶ እግር ኳስ ክለብ አራት ዓመት ተኩል ለመጫወት ተስማምቶ ፊርማውን ቢያኖርም በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ከሳምንታት በላይ ለክለቡ ሳይጫወት ጫማውን ሰቅሎ ወደ እርሻው እንዲያተኩር አስገድዶታል።

ሆኖም ስራውን ለመጀመር ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ለኮኛክ እርሻ የሚሆን መሬት ውድ እና በቀላሉ የማይገኝ መሆኑ ስራውን እንዳይጀምር ችግር ሆኖበት ነበር። ይህን እስኪያሟላም ሁለት ምግብ ቤቶችን ከፍቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

ብቸኛ ልጃቸውን በሞት ያጡ አንድ ጎረቤቱ የእርሻ መሬታቸውን የሚሸጡለት ሰው ሲያፈላልጉ ቆይተው "ልጁ ጓደኛዬ ከመሆኑም በላይ ስማችንም ተመሳሳይ በመሆኑ ይህ ገፋፍቶት ይመስለኛል እርሻውን ለኔ ሊሸጥልኝ ወሰነ" ሲል ኦሊቪዬ እርሻ ያገኘበትን አጋጣሚ ያስታውሳል።

እርሻውን የሸጡለት ዦን ሚሼል ለፒን በበኩላቸው "እዚህ ሁሉም ወይን ጠማቂ ተመሳሳይ ነው። እግር ኳስ ስለምወድ፥ ቴቢሊ ስለሚያስደስተኝና በችግሬ ወቅት ከጎኔ ስለነበር ለሱ ለመሸጥ ወሰንኩኝ።

ጥቁር ሰው እርሻዬን ቢገዛዉስ? እግር ኳስ ተጫዋች ቢሆንስ? ምንድነዉ። ብዙዎች ሊያስቆሙኝ ቢፈልጉም እኔ ግን ውሳኔዬን አልቀየርኩም" ብለዋል።

የግዢ ውሉን ተከትሎም መጀመሪያ ላይ እንደባዳ ሲታሰብ የነበረው የመጀመሪያው አፍሪካዊ የኮኛክ ጠማቂ አይን በሆነ ቦታ ላይ 22 ሄክታር የእርሻ ባለቤት ለመሆን በቃ። ከእርሻው በተጨማሪም የመጥመቂያ ባለቤት የሆነ ሲሆን የአጠማመቅ ሂደቱን በደንብ ባያውቀውም መሬቱን የሸጡለት ዦን ሚሼል አሁን አማካሪው ሆነዋል።

አጭር የምስል መግለጫ ኳስ ካቆመ ከአምስት ዓመት በኋላ የመጀመሪያውን የኮኛክ ጠርሙስ አምርቷል

የበርሚንግሃምን ቱታ ለብሶ በእርሻ ውስጥ ሲሰራ የሚታየው ቴቢሊ በእግር ኳስ ተጫዋችነቱ ዘመን በጠንካራነቱ ይታወሳል። በአንድ ወቅት በጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ከባድ ጉዳት ቢገጥመውም ጨዋታውን ከማጠናቀቁም በላይ በሌላ ጊዜ ደግሞ በአንድ እግር ጫማ ብቻ በተጫዋች ላይ ሸርተቴ ሲገባ ተስተውሏል።

"የአካባቢው ነዋሪዎች አንድ አፍሪካዊው ተጫዋች እነሱ የሚሰሩትን ለመስራት በመምረጡ በጣም ይገረማሉ። ከሰኞ እሰከ እሁድ በመስራቴም ጭምር ይደመማሉ። አግራሞታቸው የሚጨምረው ደግሞ ከባድ ስራ የሚሉትን በመስራቴ ነው።

እኔ ግን የምሰራው ሰዎችን ለማስገረም አይደለም። ስራውን ስለምወደው እስከምችለው ድረስ እሰራለሁ" ሲል እኤአ ከ1999 እስከ 2004 ለአይቮሪኮስት የተጫወተው ቴቢሊ ይገልጻል።

እንደአብዛኛዎቹ የአካባቢው የኮኛክ አምራቾች የምርቱን 90 በመቶ ለትልልቅ ኩባንያዎች የሚሸጥ ሲሆን ቀሪውን ደግሞ ኮኛኮችን ሰብስቦ በሚያስቀምጥበት ቦታ ያኖራቸዋል።

የመጀመሪያ ኮኛኩን እአአ በ2013 ያመረተው የቀድሞው ተጫዋች ምርቶቹን ለአፍሪካ ብቻ የመሸጥ ፍላጎት አለው። "ይህ ህልሜ ነው፤ ከአሁኑ ለአንዳንድ የአፍሪካ በተለይም የአይቮሪኮስት ምግብ ቤቶች ኮኛኬን እየሸጥኩ ነው።

በምፈልገው መጠን ባይሆንም በጅምሩ ደስተኛ ሆኛለሁ" ሲል ይገልጻል።

ቴቢሊ ከኮኛክ ጠመቃው ጡረታ ሲወጣ እርሻውን ለልጆቹ ማስተላለፍ ይፈልጋል፤ እስከዛ ድረስ ግን ብቸኛው አፍሪካዊ የኮኛክ አምራች ሆኖ ይቀጥላል።