''ሃገሪቷ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ነገር በጣም ደስተኛ ነኝ''

አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ
የምስሉ መግለጫ,

በርካቶች እጃቸውን ወደላይ አንስተው የ'X' ምልክት በመስራት የተቋሞ ምልክት አድርገው ይጠቀሙበታል።

አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ከዓመት በፊት ተካሂዶ በነበረው የሪዮ ዴ ጄኔሮ ኦሊምፒክ ላይ በተሳተፈበት የማራቶን ውድድር መጨረሻ ላይ እጆቹን ወደ ላይ አንስቶ የኤክስ ምልክት በመስራት በመንግሥት ላይ ያለውን ተቃውሞ መግለፁ ይታወሳል።

ከዚያ ቅፅበት በኋላ ነበር የበርካቶችን ቀልብ መሳብ የቻለው። በሪዮ ኦሊምፒክ ላይ ባሳየው ተቃውሞ ከበርካቶች ዘንድ ድጋፍ ተችሮት ነበር።

በኦሊምፒክ ውድድሩ ላይ ይህን ለመፈፀም ኢትዮጵያም እያለሁ አስብ ነበር። ከዚህ በፊት ከሌሎች አትሌቶች ጋር ስለሃገሪቷ ፖለቲካዊ ሁኔታ ለመወያየት ስሞክር ብዙ ጊዜ ለመወያየት ፍቃደኛ አይሆኑም ሲል ይናገራል።

''የሥርዓቱን መጥፎነት ከልጅነቴ ጀምሮ ስመለከት ነው ያደኩት። ገና ትምህርት ቤት ሳልገባ ሰዎች በአደባባይ ሲደበደቡ እመለከት ነበር። ወላጅ አባቴም ሥርዓቱን ይቃወም ነበር። እንግዲህ ከልጅነቴ ጀምሮ ታምቆ የነበረው ነው ድንገት ፈንድቶ ይህን ሁሉ እንዳደርግ ብርታት የሆነኝ'' ይላል ፈይሳ።

ከአትሌትነት ወደ ''ሰዓዊ መብት ተሟጋችነት''

ከሪዮ በኋላ በሚሳተፍባቸው ውድድሮች መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ ፈይሳ አጆቹን ወደላይ በማንሳት የኤክስ ምልክት በመስራት መልዕክቱን ያስተላልፋል። ይህን ባደረገ ቁጥርም የሚሰማው ደስታ ከፍተኛ ነው።

''ይህን ሳደርግ የንዴት፣ የሃዘን፣ የደስታ እና የጥንካሬ ስሜት በአንድ ላይ ሰውነቴን ይወረዋል ይህም ብርታት ይሰጠኛል'' ሲል ይናገራል።

ፈይሳ እንደሚለው ሪዮ ላይ የፈፀመው ተግባር እሱን ታዋቂ ከማድረጉ ይልቅ፤ ሃገሪቷ የምትገኝበትን ፖለቲካዊ ሁኔታ የተቀረው ዓለም ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል ይላል።

ዛሬ ላይ ፈይሳ አትሌት ብቻ አይደለም። ብዙዎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሚል ሌላ ስም ሰጥተውታል። በውድድር ቦታዎች እና በተጋበዘባቸው መድረኮች የተለመደ ምልክቱን ያሳያል። እንዲሁም ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸውን መልዕክቶች ያስተላልፋል።

''ከሃገር ቤት ስወጣ ይዤ የወጣሁት እጅ እና እግሬን ብቻ ነው። በምሳተፍባቸው የሩጫ ውድድሮች ባሸንፍም ባላሽንፍም በእጄ የኤክስ ምልክትን በመስራት የተቃውሞ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ'' ሲል ይናገራል።

ፈይሳ ሌሊሳ በዚህ ተግባሩ የበርካታ ዓለም-አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ መሳብ ችሏል።

እሱ እንደሚለው ''በምፈፅመው ተግባር ብዙዎች እኔን እንደ ፖለቲከኛ ይመለከቱኛል እኔ ግን ይህን አልቀበልም'' ይላል።

''እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም። የፖለቲካ ተሳትፎም የለኝም። የእኔ አካል የሆነው ህዝብ ግን ሲገረፍ፣ ያለፍትህ ሲታሰር እና ሰብዓዊ መብቱ ሳይጠበቅ ሲቀር ማየት ስለማያስችለኝ መላው ዓለም የምንገኝበትን ሁኔታ እንዲረዳ ይህን ተግባር ለመፈፀም ችያለሁ'' ይላል።

የአሜሪካ ኑሮ

አትሌት ፈይሳ ኑሮውን በአሜሪካ ካደረገ አንድ ዓመት አስቆጥሯል። ከሃገር መውጣቱ ብዙ ነገሮችን ቢያሳጡትም ''በፈፀምኩት ተግር አልፀፀትም'' ይላል።

''እውነት ለመናገር የቀድሞ ህይወቴ የሚናፈቅ ነው። ይሁን እንጂ ይህን ተግባር ከፈፀምኩ በኋላ ይህ ሊከሰት እንደሚችል ስለማውቅ ያን ያህል አልከበደኝም'' ሲል ፈይሳ ያስረዳል።

የምስሉ መግለጫ,

ቤተሰቦቹ ወደ አሜሪካ ከመምጣታቸው በፊት በነሱ ላይ ሊደርስ የሚችለው ነገር እጅግ ያሳስበው ነበር።

ድሮ ይመላለስባት የነበረች እና አሁን ላይ ቋሚ መኖሪያው የሆነችው አሜሪካ ለእሱ እና ለባለቤቱ ብዙ ባትመችም ''ልጆቼ ግን በደስታ እየኖሩ ናቸው'' ሲል ይናገራል።

ፈይሳ ከጥቂት ወራት የብቸኝነት ኑሮው በኋላ ቤተሰቦቹ ወደ አሜሪካ መጥተው በደስታ እየኖረ እንደሚገኝ ይናገራል።

የአሜሪካ ህይወት ከኢትዮጵያ ኑሮ እጅግ የተለየ እንደሆነ የሚናገረው ፈይሳ ''ልጆቼን ትምህርት ቤት ወስጄ የምመልሰው እና አስቤዛ የምገዛው እኔ ነኝ። የውሃ፣ የመብራት እና የትምህርት ቤት ክፍያ ደረሰኞች ሳገላብጥ ነው የምውለው። እንዲያው ትምህርት ቤት ሳለሁ በሚገባ ባጠና ኖሮ እንዲህ ባልከበደኝ እያልኩ እራሴ ላይ እቀልዳለሁ'' ይላል።

ፈይሳ ወደ አሜሪካ ከመጣ በኋላ የኑሮው ዘይቤ ብቻ ሳይሆን አስተሳሰቡም እንደተቀየረ ይናገራል። ''ዛሬ ላይ ጉዳዬ አትሌቲክስ ብቻ አይደለም። በሃገር ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ በአትኩሮት እከታተላለሁ'' ሲል ያስረዳል።

''ሃገሪቷ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ነገር በጣም ደስተኛ ነኝ። ከአንድ ወር በፊትና ዛሬ ላይ ተኝቼ የማድረው እንቅልፍ የተለያየ ነው'' የሚለው አትሌት ፈይሳ፤ በአሁኑ ሰዓት ህዘቡ የተሻለ የአንድነት መንፈስ ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሶ፤ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ የሌለው ደግሞ በሃሳብ ህዝቡን ለመርዳት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያደንቅ ያስረዳል።

ሃገሬን መቼ ጠላ?

በሪዮ ካሳየው ተቃውሞ በኋላ የብዙዎቹ ጥያቄ ለየትኛው ሃገር ነው ተሰልፎ የሚወዳደረው የሚለው ነበር።

ለጊዜው የትኛውንም ሃገር ወክዬ እየተወዳደርኩ አይደለም። ሃገሬን እወዳለሁ በተጠየኩ ጊዜም ለመሮጥ ዝግጁ ነኝ ይላል።

''የማስመዘግበው ፈጣን ሰዓትን መሰረት አድርገው መምረጥ የሚችሉት እነሱ ናቸው። ከተመረጥኩ በውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን ወክዬ ለመሮጥ ደስተኛ ነኝ። እኔ ሃገሬን መቼ ጠላሁ?'' ሲል ፈይሳ ይጠይቃል።

የምስሉ መግለጫ,

አትሌት ፍይሳ በሄደኩበት ሁሉ የተቃውሞ ምልክቱን በማሳየት የህዝቡን ብሶት ሁሉም እንዲረዳ ጥረት አደርጋለው ይላል።

እዚህ ከቀረሁ በኋላ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሃላፊዎች አናግረውኝ አያውቁም። ''ሊያናግሩኝም ሆነ ለውድድር ሊመርጡኝ እንደማይችሉ እርግጠኛ ነኝ'' የሚለው ፈይሳ፤ በሪዮ ኦሊምፒክ ሁለተኛ በመውጣቱ መሸለም ይገባው የነበረን ወደ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ማበረታቻ ሽልማት እንዳልተሰጠው ይናገራል።

''ለቤተሰቦቼ ምንም አይነት መልዕክት አላኩም እኛም አልጠየቅንም ገንዘቡም በዛው ቀረ'' ሲል ያስረዳል።

ይሳ የአትሌቲክስ ውጤት ለምን ቀነሰ?

ፈይሳ አሪዞና በምትባለው የአሜሪካ ግዛት ውስጥ የሚኖር ሲሆን፤ የግዛቲቱ የመሬት አቀማመጥ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን እና ለልምምድ ምቹ እንደሆነ ይናገራል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚያስመዘግበው ውጤት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ደካማ እንደሆነ የሚናገረው አትሌት ፈይሳ፤ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያስቀምጠው አሰልጣኝ እና አብረውት ለልምምድ የሚወጡ አትሌቶች አለመኖራቸው ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ቀነኒሳ በቀለ እና ፈይሳ ሌሊሳ

ፈይሳ እና ቀነኒሳ

ቀነኒሳን እንደ አርዓያው አድርጎ ወደ አትሌቲክሱ ዓለም እንደገባ የሚናገረው ፈይሳ፤ ለሃገር አቋራጭ ውድድር ልዩ ፍቅር እንዳለው ይገልፃል።

በልምምድ ወቅት ''ሰዎች አንተ ልክ እንደ ቀነኒሳ ነው የምትሆነው'' ሲሉኝ እጅግ እደሰት እና ብርታትም አገኝ ነበር ይላል። አሁንም ለቀነኒሳ ልዩ ፍቅር አለኝ ሲል ስሜቱን ይገልፃል።

ፈይሳ መንግሥትን ተቃውሞ ወደ ሃገር ሳይመለስ መቅረቱ፤ ቀነኒሳ ደግሞ ስፖርት እና ፖለቲካ ለየቅል ናቸው ብሎ በሰጠው አስተያየት ብዙዎች በተለያየ መነጽር ተመልክተዋቸው ነበር።

ፈይሳም እንደሚለው ቀነኒሳ ይህን አስተያየት በሰጠበት ወቅት ቅሬታ ተሰምቶት ነበር።

የተቃውሞ ምልክቱን ካሳየ በኋላ የእሱን ፈለግ የተከተሉ አትሌቶች እንዳሉ የሚናገረው ፈይሳ፤ አሁንም በርካታ አትሌቶች ውስጣቸው ያለውን ሰሜት በሆዳቸው ይዘው አንጂ የእሱን ስሜት እንደሚጋሩ ያምናል።