ካለሁበት 7፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ካምቦዲያ መኖር እፈልግ ነበር

የአክሊል ቀን በባልኮኒዋ ላይ ተቅምጣ የኢትዮጵያን ቡና በማጣጣም ይጀምራል Image copyright Aklile Mekuria
አጭር የምስል መግለጫ አክሊል ቀኗን በረንዳዋ ላይ ተቀምጣ የኢትዮጵያን ቡና በማጣጣም ትጀምራለች

ስሜ አክሊል መኩሪያ ይባላል የተወለድኩት ከኢትዮጵያዊያን እናትና አባት ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ ነው።

ሰባት ዓመት ሲሞላኝ ኑሯችንን ወደ ኢትዮጵያ መልሰን ለአስራ ሁለት ዓመታት እዚያ ቆየሁ። በኋላም ለሦስት ዓመታት በሕንድ ከቆየሁ በኋላ ወደ ሀገር ቤት ተመለስኩ። ለጥቆም ለተወሰነ ጊዜ ያህል ኑሮዬን ሩዋንዳ አደረኩኝ። አሁን የምኖረው ግን በካምቦዲያ ሁለተኛ ከተማ በሲየም ሪፕ ነው።

አባቴ ያወራልኝ በነበሩት ታሪኮች ምክንያት የካምቦዲያ ታሪክና ሀገሪቱ በጣም ይስቡኝ ስለነበር ከልጅነቴ ጀምሮ ካምቦዲያ መኖር እፈልግ ነበር።

ሆኖም ግን ሲየም ሪፕን እስክጎበኝና የሰውን እንግዳ ተቀባይነትም ሆነ የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት እስክመለከት ድረስ መወሰን አልቻልኩም ነበር። አንዴ ከወሰንኩ በኋላ ደግሞ በደንብ መዘጋጅት ብቻ ነበር የሚያስፈልግኝ።

ሥራ እያፈላለኩ ሳለ ለኮሚኒኬሽንና ፈንድ አሰባሳቢ ኃላፊነት ክፍት የሥራ ቦታ እንዳለው ለሚያስትዋውቅ መንግሥታዊ ላልሆነ ድርጅት አመለከትኩ ሥራውንም ወዲያው አግኝቼ ይኸው አሁን እዚህ ነኝ።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የካምቦዲያ ሰዎች

ለእኔ ሲየም ሪፕ ከአዲስ አበባ አንፃር በጣም ሰብዓዊ ከተማ ናት። ይህን የምለው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሰብዓዊ ስላልሆኑ ሳይሆን የሲየም ሪፕ ነዋሪዎች ለቁጣና ለጥል የዘገዩ ስለሆኑ ነው። ለዚህ ሀገር ነዋሪዎች ጭቅጭቅ ምንጊዜም የመጨረሻ አማራጭ ነው። ሁልጊዜ አስቀድመው ለንግግርና ለውይይት ቅድሚያ ይሰጣሉ፤ ደግሞም ሰውን በመረዳት አለመግባባትን ለማስወገድ ዝግጁ ናቸው።

ካምቦዲያ ከኢትዮጵያ የምትለይበት ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ለእኔ በጣም የተቀየረብኝና የተለየብኝ ነገር ቢኖር ምግቡ ነው። ሕንድ ውስጥ እኖር በነበረበት ጊዜ ከምመገበው ጋር ሩዙና እርዱ ትንሽ ቢመሳሰልም በአብዛኛው ግን ልዩነቱ የሰፋ ነው። እስካሁንም መልመድ አቅቶኛል። ምግቦቻቸውን ብዙም ባላዘወትርም ከሁሉም አሞክ ከሪ የሚሉትን የኮኮናት ወተትና ብዙ አትክልቶችን የያዘውን ምግብ እወደዋለሁ። እኔ ምግብ ስሠራ ደግሞ በርበሬና ሚጥሚጣ በመጨመር የራሴን የተለያዩ የምግብ አይነቶች አዘጋጃለሁ፤ ለምሳሌ በሽሮ ፋንታ የሽምብራ ወጥ እሰራለሁ።

Image copyright Aklile Mekuria
አጭር የምስል መግለጫ በግራ አሞክ ከሪ ከሬስቶራንት፣ በቀኝ የአክሊል ሽምብራ ወጥ "በሽሮ ፋንታ"

አንዳንዴ ሀገሬ ትናፍቀኛልች። ምን ይናፍቅሻል ብባል ይህን ሊያነቡት ስልሚችሉ እናቴና አባቴ ማለት ይኖርብኛል። ቀልዱ እንዳለ ሆኖ ግን ለመግለፅ ከበድ ቢልም የሚናፍቀኝ የማወቅ ችሎታዬ ነው። ምክንያቱም እዚህ ምንም ነገር አላውቅም። የምሄድበትንና እየተፈጸሙ ያሉ ነገሮች ብዙውን ጊዜ ያደናግሩኛል። አዲስ አበባ የራሴ እንደሆነች ይሰማኛል ምክንያቱም እንደራሴ ነው የማውቃት። እዚህ ግን ብዙውን ጊዜ ከሰው ድጋፍ ስለምሻ ትንሽ ብስጭት ያደርገኛል።

የምኖረው ከመንገድ ዳር ባለ አፓርትማ ሲሆን ከፊት ለፊት ወዳለው ወንዝ እይታን የምትጋብዝ አነስ ያለች በረንዳ አለችኝ። ብዙውን ጊዜ ከኢትዮጵያ ያመጣሁትን ቡና ይዤ ቁጭ ብዬ የሚፈጠሩትን ነገሮች እንደ ቴሌቪዥን መመልከት ደስ ይልኛል። በቅርቡ ለሚደረገው የውሃ በዓል የሚወዳደሩትን መርከበኞች ሲለማመዱ፣ ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆች፣ ወደ ሥራ የሚራወጡትንና ዕለተለት ኑሮዋችውን የሚገፉትን ሰዎች ስመለከት ማንም ሳያየኝ ምድር ስትሽከረከር የምመለከታት ያህል ነው የሚስማኝ።

Image copyright Aklile Mekuria
አጭር የምስል መግለጫ በግራ 'ቀኔን ስጀምር'፣ በቀኝ ከመተኛቴ በፊት በበረንዳዬ በኩል እይታዬ

ሲየም ሪፕ ከመጣሁ አንስቶ እስካሁን በጣም አስደሳች የምለው ገጠመኝ...የምኖርበት ቤት ማግኘቴ ነው። ይህን የመሰለ እይታ ያልውን ቤት ከማግኘቴ በፊት ለተከታታይ ሳምንታት ከሻንጣዬ ጋር ብቻ ነበርኩ። ብዙ ቤቶችን አፈላልጌ ካየሁ በኋላ ነበር በድንገት ብዙ ስለምትጓዝ ደባል ትፈልግ የነበረችን መልካም ሴት አግኝቼ እዚህ የተሟላ ቤት የገባሁት። የራሴ ቤት ያለሁ ያህል ስለተሰማኝ በገባሁ በመጀመሪያው ቀን ነበር ምግብ የሠራሁት።

Image copyright Aklile Mekuria
አጭር የምስል መግለጫ አክሊል ምግብ እየሠራች

በሲየም ሪፕ የአንግኮር ቤተ-መቅደስ ስላለ ለካምቦዲያ ዋነኛዋ የጉብኝት ከተማ ናት። እነሱንም ለማየት ለግማሽ ቀን ብቻ የሚመጡ ሰዎች ስላሉ የኑሮ ልዩነት ጎልቶ ይታያል። ብዙ ጎብኚዎች ቢመላለሱባትም ለነዋሪዎቹም ሆነ ለቤተ-መቅደሶቹ ክብር እንደሌላችው ማየቱ ድግሞ ያሳዝናል።

ሀገሪቱንም ሆነ ሰዎቹን ለማወቅ ጥረት የሚያደርግ ጎብኚ የለም በዚያ ላይ ሰዎቹ ዓይናፋር በመሆናችው ምንም ነገር አይናገሩም። የሚመጡት ቱሪስቶች ከተማዋን በክለው ይሄዳሉ፤ ነዋሪዎቹ ደግሞ በውጤቱ ተጎጂ ይሆናሉ። ይህንን መቀየር ብችል ደግሞ ደስ ይልኛል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ቴምፔሎቹ ዋና የቱሪዝም ቦታዎች ናችው

የዓለም ሕዝብ ስለኢትዮጵያና ስለካምቦዲያ ያላቸው የተሳሳቱ አመለካከቶች ሁለቱም ሀገራት በአንድ ዓይነት መንገድ ላይ እንዳሉ ይሰማኛል። ለኢትዮጵያ ድርቅ ሲሆን ለካምቦዲያ ደግሞ ጦርነት ነው። እነዚህ የተሳሳቱ እመለካከቶች ስለሀገሪቱ ሊኖር የሚችለውን ግንዛቤ ሊቀይር ቢችልም ግን ነዋሪዎቹ የተጫነባቸውን ያለፈ ታሪክ ለመወጣት እየሠሩ ማየቱ ያስገርማል።

የካምቦዲያ ሰዎች ስለራሳችው ማውራት ያስደስታቸዋል። ስለባህላችው ስለታሪካችውና ሲያነሱ በሀገሪቱ ስም ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ስላለፈው ዘር ማጥፋትም በላይ እንደሆኑ ያሳያሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ በበቆጂ ከወጣቶች ጋር እሰራ በነበረበት ጊዜ የነበሩትን የተሳሳቱ አመለካከቶችን አልፈው ሕይወትን ለማሽነፍ ሲሠሩ ማየት ያስደንቀኝ ነበር። እዚህ ያሉትም ወጣቶች ተመሳሳይ ናችው፤ ምክንያቱም ለለውጥ ተጠምተዋል። ሁለቱም ሀገራት ከተጫኑባቸው የአንድ ወቅት አስከፊ ክስተቶች ለመላቀቅ ጠንክረው እየሠሩ ስለሆኑ በውስጡ ሆኜ ማየቴ ያስደስተኛል።

እዚህ ከመጣሁ የከበደኝ ነገር ቢኖር በሥራ ቦታዬ ያለው ጫና ብቻ ነው። ነገር ግን እሱንም ቢሆን እየተማርኩበት ስለሆነ እወደዋለሁ። እያሳለፍኳችው ያሉትን ፈተናዎችን ለመወጣት፤ እራሴን ይህ የዕድገት መንገድ እንደሆነ እያሳመንኩት እገኛለሁ።

በእነዚህ ውጣውረዶች መካከል ቁጭ ብዬ እራሴን ኢትዮጵያ ባገኘው የት እንደምሆን ሳስብ መስቀል አደባባይ እንደምሆን ይሰማኛል። ለምን ብባል ፀሐይዋ ስትጠልቅ፣ ባቡሩ ሲያልፍ፣ ከሥራ የሚመለሰውንና የአካል ብቃት ልምምድ የሚያደርጉትን ስዎች ለማየት ስል ነው የሚሆነው። እንዳንድ ሰዎች ቀናችውን ለመቋጨት ሌሎች ደግሞ ምሽታት ሕይወታቸውን ለመጀምር ይተላለፋሉ። እኔ በመስቀል አደባባይ ነው ሁሉን ነገር የማየው።

Image copyright Aklile Mekuria
አጭር የምስል መግለጫ አክሊል በሲየም ሪፕ በረንዳዋ ላይ ቀኗን ስትቋጭ

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገረቻት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦

ካለሁበት 8፡ ኢትዮጵያዊው የበረዶ ሸርተቴ ተወዳዳሪውና አስተማሪው በጃፓን

ካለሁበት 9፡ በኑሮዬ ደስተኛ ብሆንም ለቁርስ ቋንጣ ፍርፍር ባገኝ እወዳለሁ

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ