በአምቦ ከተማ በተከሰተ ግጭት ሰዎች ተገደሉ

የተቃጠሉ መኪኖች
አጭር የምስል መግለጫ በግጭቱ ቢያንስ 10 ሰዎች እንደተገደሉ የአይን እማኞች ይናገራሉ

በስልክ ያነጋገርናቸው የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች እንደነገሩን ስኳር ጭነው በከተማው የሚያልፉ መኪኖች እንዳሉ መረጃ ለአካባቢው በመድረሱ ፤ መኪኖቹን ለማስቆም በመጠባበቅ ከትናንት ጀምሮ መንገድ መዝጋት ጀምረው ነበር።

ምክንያታቸው ደግሞ በሀገሪቱ የሚታየው የስኳር እጥረት በአምቦም የሚስተዋል መሆኑ ነው።

በከተማዋ አንድ ኪሎ እሰከ 70 ብር ድረስ ይሸጣል ይላሉ።

እናም በዚህ ሁኔታ ስኳር ተጭኖ ወደሌላ ቦታ መሄዱን በመቃወም ነው መንገድ መዝጋት የጀመሩት።

''ከተማዋን አቆርጠው የሚሄዱ ዋናና መጋቢ መንገዶች በመዘጋታቸው የክልሉ ፖሊስና እኛ ሆነን ሊያልፍ የነበረውን ስኳር ስንጠብቅ አድረናል'' ይላሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለገ አንድ የአካባቢው ነዋሪ።

ሃሙስ ዕለት ከማለዳው አንድ ሰዓት አካባቢ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት መለያ የለበሱ በተቃዋሚዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።

"እኔ በአይኔ ያየሁት አምስት ሰዎች ሲገደሉ ነው።ግን የሞቱት በጣም በርካታ ሰዎች ናቸው'' ያለን ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ነው።

''ሁለት የፌደራል ፖሊስ ልብስ የለበሱ በድንጋይ ተደብድበው እንደሞቱ አይቻለሁ'' ብሎናል።

ቢቢሲ ግን የሟቾቹን ትክክለኛ ቁጥር ለማረጋገጥ አልቻለም።

ከግጭቱ ጋር ተያይዞ በንብረት ላይም ጉዳት የደረሰ ሲሆን የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ንብረት የሆኑ ሁለት የጭነት መኪናዎች መቃጠላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

አጭር የምስል መግለጫ በከተማዋ ስኳር እንዳይዘዋወር መንገዶች እንዲህ ተዘግተዋል

የአሮሚያ ክልል የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ በፌስ ቡክ ገጻቸው የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉንና በሌሎች ሰዎች ላይም የአካል ጉዳት መድረሱን የሚገልጽ መረጃ አስፍረዋል።

''ከሰላማዊ ሰልፍና ከስኳር ፍተሻ ጋር በተያያዘ ወጣቶችን በማነሳሳትና ሥርዓት አልበኝነት እንዲስፋፋ በማድረግ ለግጭቱ መንስዔ የሆኑትን አካላትን እናወግዛለን'' ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት ከተማዋ በአንጻራዊነት የተረጋጋች ትመስላለች፤ ነገር ግን መንገዶች እንደተዘጉ ሲሆን ሰልፈኞቹም ወደየቤታቸው አልተመለሱም።

ከዚህም የተነሳ ብዙዎች አሁንም ተጨማሪ ጉዳት ሊደርስ የሚችል ስጋት እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች