ካታሎንያ ነጻ ሀገርነቷን ስታውጅ ስፔን ደግሞ የቀጥታ አገዛዝ እንዲተገበር ወስናለች

ምርጫው በሚካሄድበት ጊዜ ደጋፊዎች ከፓርላማው ፊት ለፊት ተሰባስበው ነበር Image copyright Getty Images

የካታሎንያ ግዛት ፓርላማ ነጻ ሃገርነቷን ባወጀ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የስፔን መንግስት በበኩሉ የቀጥተኛ አገዛዝ ስርዓትን ለመተግበር ወስኗል።

ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ያገለሉበት የካታሎንያ ፓርላማ ውሳኔ በ70 ድጋፍና በ10 ተቃውም ጸድቋል።

የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያኖ ራጆይ በካታሎንያ ዴሞክራሲና መረጋጋትን ለማስፈን የቀጥተኛ አገዛዝ መተግበር ያስፈልጋል ብለው ነበር።

ዛሬም የስፔን ህግ አውጪ ምክር ቤት በግጭት ወቅት ግዛቲቱን እንዲቆጣጠር የሚፈቅደውን የህገመንግስት አንቀጽ 155 ተግባራዊ ለማድረግ ወስኗል።

ይህ ደግሞ ማድሪድ የካታሎኒያ መሪዎችን አባራ የፋይናንስ፣ የፖሊስና የመገናኛ ብዙኃንን ለመቆጣጠር ያስችላታል።

ባለፈው ወር ግጭቱ የተጀመረው ካታሎናውያን በሕዝበ-ውሳኔ ከስፔን ነጻ ለመውጣት የሚያስችላቸውን ድምጽ ከሰጡ በኋላ ነው።

የካታሎንያ መንግስት ከ43% ድምጽ ሰጪዎች 90 % የሚሆኑት ነጻነትን መርጠዋል ብሏል።

ሆኖም የስፔን ህግመንግስታዊ ፍርድ ቤት ህዝበ ውሳኔውን ውድቅ አድርጎት ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች